Logo
FIDEL POST NEWS
የሜንዲ ፎጣ፦ ከዋንጫው በላይ የታደነችው ብርቅዬ ንብረት

​በካዛብላንካ ስታዲየም ውስጥ የነበረው ድባብ ከእግር ኳስ ጨዋታ ይልቅ፣ የጠፋ ንብረትን ለማስመለስ የሚደረግ የፖሊስ ፍለጋ ይመስል ነበር። ጨዋታው እንደተጀመረ የሞሮኮው አጥቂ ብራሂም ዲያዝ ወደ ሰኔጋል ጎል ሲቃረብ፣ የስታዲየሙ ደጋፊዎች አይን ኳሱ ላይ ሳይሆን ጎሉ ውስጥ በተሰቀለው ፎጣ ላይ ነበር።

ሞሮኮዎች በልባቸው "ሜንዲ ጎል እንዳይገባበት ያደረገው ግርግዳ ሳይሆን፣ ይሄ ፎጣ ውስጥ ያለው ድግምት ነው" ብለው አምነዋል።

​በጨዋታው አጋማሽ ላይ አንዱ የኳስ አቀባይ ህጻን፣ ልክ እንደ 'ሚሽን ኢምፖሲብል' ተዋናይ በረኛው ሜንዲ ፊቱን ለማየት ወደ ሌላ አቅጣጫ ሲዞር በዝግታ ተንፏቆ መጣ። ልክ ፎጣውን ነክቶ ሊፈረጥጥ ሲል ግን፣ ያልታሰበ አደጋ ገጠመው። የሰኔጋል ተጠባባቂ በረኛ ዬቫን ዲዩፍ፣ ልክ እንደ አፍሪካ አንበሳ ከሞቅታው መንንጭቶ በመነሳት ህጻኑን አየር ላይ አቆመው።

​"ወዴት ነው የምትወስደው?" የሚል ይመስላል የዲዩፍ አይን። ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ጨዋታው በሁለት ተከፈለ። ሜዳው ውስጥ ሜንዲ ኳስ ይከላከላል፤ ከሜዳ ውጭ ደግሞ ዲዩፍ ፎጣውን ይከላከላል። ዬቫን ዲዩፍ በዛ እለት ከሰኔጋል መከላከያ ሰራዊት በበለጠ ንቁ ነበር። ፎጣውን አጥፎ ደረቱ ላይ አጣብቆ ይዞት፣ ማንም እንዳይነካው እንደ ውድ ሀብት ይጠብቀው ጀመር።

​ሞሮኮዎች ስልታቸውን ቀየሩ። አሽራፍ ሀኪሚ ሳይቀር ወደ መስመር መጥቶ "እባክህ ፊቴን ልጥረግበት" በሚል የሽንገላ ጥያቄ አቀረበ። ዲዩፍ ግን "ይህ ፎጣ የሰኔጋል ብሄራዊ ክብር ነው፤ በላቡ ካልሆነ በስተቀር በሞሮኮ እጅ አይነካም" የሚል በሚመስል ጽናት ፊቱን አዞረበት።

​ሁኔታው ያስቃቸው የነበሩት የናይጄሪያው በረኛ ንዋባሊ ደጋፊዎች ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ "ፎጣው ድግምት የለውም፣ ሞሮኮዎች ግን ሳሙና ስለሌላቸው ሊሰርቁት ነው" እያሉ ይቀልዱ ነበር።

​በመጨረሻም ሰኔጋል 1 ለ 0 አሸንፋ ዋንጫውን ስትቀዳጅ፣ ዲዩፍ ዋንጫውን ለመቀበል ሲሄድ ፎጣውን አልጣለውም ነበር። እንዲያውም በድል ማግስት ዲዩፍ በኢንስታግራም ገጹ ላይ የሜዳሊያውን እና የፎጣውን ፎቶ ለጥፎ "ለፎጣው ብዬ የተጋደልኩትን ያህል ለዋንጫው አልተጋደልኩም" የሚል መልዕክት አስተላልፏል።

​አሁን ላይ በሞሮኮ ገበያ ውስጥ "የሜንዲ ፎጣ" የሚሉ ሀሰተኛ ፎጣዎች በውድ ዋጋ እየተሸጡ እንደሆነ ይነገራል፤ ትክክለኛው ፎጣ ግን በሰኔጋል ቤተ-መዘክር ውስጥ "ሞሮኮን ያስለቀሰችው ጨርቅ" ተብሎ ሊቀመጥ ጥቂት ቀርቶታል።
7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.