Logo
FIDEL POST NEWS
ዳቺ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሸጉ የጥራጥሬ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ ጀመረ


የዳቺ የምግብ ማቀነባበርያ አክሲዮን ኩባንያ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ የተመረቱ የታሸጉ የባቄላ እና የቦሎቄ ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አስታወቀ።

​ዛሬ ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል በተከናወነ ልዩ መርሐግብር፣ ኩባንያው ከኢትዮጵያ ገበሬዎች የተገኙ ምርቶችን እሴት በመጨመር (Agro-processing) ለገበያ ማቅረቡን ይፋ አድርጓል።

ይህም ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ የታሸጉ ምግቦችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካትና (Import Substitution) የውጭ ገበያ ላይ ያተኮረ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማጠናከር በምታደርገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።

​ዳቺ በአሁኑ ወቅት ስድስት ዓይነት ምርቶችን ማለትም ቀይ፣ ነጭ እና ጥቁር ቦሎቄን፣ ፉልን (ባቄላ)፣ አተርን እና ጣፋጭ በቆሎን (Sweet Corn) በ400 ግራም እሽግ ማምረት የጀመረ ሲሆን፣ ምርቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ቀርበዋል። በቅርብ ወራት ውስጥም የ3 ኪሎ ግራም እሽጎች ለገበያ እንደሚቀርቡ ተገልጿል።

​የዳቺ ዋና የንግድ ኃላፊ  ቢኒያም ዮሐንስ እንደተናገሩት፣ ምርቶቹ ዓለም አቀፍ የጥራትና የደህንነት መመዘኛዎችን የሚያሟሉ ሲሆን በቅርቡ ዱባይን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ዓለም አቀፍ ገበያዎች የሚላኩ ይሆናል። "አዳዲሶቹ ምርቶች ኢትዮጵያ በዓለም የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ያላት ሚና ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወደ ተጠናቀቀ ምርት ላኪነት እየተቀየረ መሆኑን አብሳሪ ናቸው" ሲሉ ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።

​ዳቺ የምግብ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት አራት ፋብሪካዎችን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ የታሸጉ ምግቦችን፣ የቲማቲም ድልህን፣ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን፣ ጃም፣ ማዮኔዝ እና 26 ዓይነት የቅመማ ቅመም (Condiment) ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛል። ኩባንያው በአሁኑ ወቅት የሚያቀርባቸውን 36 ዓይነት ምርቶች ወደፊት ወደ 100 ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።
7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.