Logo
FIDEL POST NEWS
ሽጉጥ አውጥቶ በማስፈራራት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈጸመው የፖሊስ አባል 16 ዓመት ተፈረደበት።

ዋና ሳጅን አሸናፊ ኡኩሞ በወላይታ ዞን ባይራ ኮሻ ወረዳ የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ናቸው።

ዋና ሳጅን አሸናፊ ኡኩሞ በፈፀሙት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በ16 አመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የወላይታ ሶዶ ፖሊስ መመሪያ አዛዥ ኮማንደር ሀብታሙ አሰፋ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አሳውቀዋል።

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመዉ በቀን 5/1/2018 ዓ.ም ዕለተ ሰኞ በግምት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ነው።

የግል ተበዳይ በሶዶ ከተማ አስተዳደር ወደ አጎቷ ቤት በእግር እየመጣች ባለችበት ዋና ሳጅን አሸናፊ  " በሞተር ልሸኝሽ " በማለት ካሳፈራት በኋላ ፔንስዮን ይዟት ይገባል።

በኃላም ሽጉጥ አዉጥቶ በማስፈራራት አስገድዶ መድፈሩን በፖሊስ ምርመራና በዐቃቤ ህግ ተረጋግጧል።

በሶዶ ከተማ አስተዳደር የሚገኘዉ የአራዳ ሴቶችና ህጻናት ልዩ ችሎት በተከሳሽ ላይ የቀረበውን ክስ ጥፋተኛ ነው ሲል በ16 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

ከዚሁ የጉዳይ ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ሚዲያዎች " ፖሊስ ባልደረባው የሰራውን ወንጀል ለመሸፈን ሞክሯል " የሚሉ ሀሳቦች ሲዘዋወሩ ነበር።

የወላይታ ሶዶ ፖሊስ መመሪያ አዛዥ ኮማንደር ሀብታሙ አሰፋ ግን " ይህ ፍጹም መሰረተ ቢስ እና አግባብነት የሌለው ነው " ብለዋል።

" አንዳንድ ጥላቻ የሚሰብኩ ሚዲያዎች የግለሰቡን ጥፋትና ወንጀል የመላዉ ፖሊስ ተግባር በማስመሰል ሲያቀርቡም ነበር ይህም መሰረተ ቢስ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

" እንዲህ እያሉ ያሰራጩትን እንጠይቃቸዋለን " ብለዋል።

" ፖሊስ እኮ ግለሰቡን አስሮ የምርመራ መዝገብ ከማደራጀት እስከ የዐቃቤ ሕግ ምስክርና የፖሊስ አባል ሆኖ ይህን አስነዋሪ የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን በክስ ማክበጃነት እንዲነሳ የድርሻቸውን ሁሉ ተወጥቷል " ብለዋል።

" ከዚህ ባለፈ የዉሳኔዉን ችሎት በሚዲያ እንዲዘገብ ያደረገው እራሱ ፖሊስ ነው ይህ በሆነበት የተቋሙን ገፅታ ለማበላሸት የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው " ሲሉ አሳስበዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
#tikvahethiopiafamilyhawassa

tikvahethiopia
5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.