Logo
FIDEL POST NEWS
በኢራን በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተሰማ

​በአሁኑ ወቅት በኢራን እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ እ.ኤ.አ. በ2022 ከነበረው የማህሳ አሚኒ ተቃውሞ ወዲህ ትልቁ ነው።

​ካለፈው እሁድ ጀምሮ በኢራን በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ቢያንስ ስድስት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። የአሜሪካው ፒቢኤስ (PBS) ቻናል እንደዘገበው ከሆነ፤ አምስት ሰዎች ሐሙስ ዕለት ሲሞቱ አንዱ ደግሞ ረቡዕ ዕለት ተገድሏል።

​የሲኤንኤን የዜና ወኪል በበኩሉ በሐሙስ ዕለቱ ተቃውሞ ቢያንስ 3 ሰዎች ሲገደሉ 17 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ብሏል።

​የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በሐሙስ ዕለቱ ግጭት የተገደሉት ሁሉም ሰዎች ተቃዋሚዎች ናቸው።

ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ ከሟቾቹ መካከል ሦስቱ የተገደሉት በምዕራብ ኢራን በሚገኝ የአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት በተሰነዘረበት ወቅት ነው።

​የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፤ የኢራን ሥርዓት ተቃውሞዎችን ለመጨፍለቅ በተደጋጋሚ የሚጠቀምበት የባሲጅ ታጣቂ ኃይል አባል ረቡዕ ዕለት ተገድሏል።
​ሲኤንኤን የኢራኑን ፋርስ የዜና ወኪል ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ሐሙስ ዕለት በባለሥልጣናት ላይ ተኩስ ከፍተዋል። ይሁን እንጂ ፋርስ ላቀረበው ዘገባ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለማቅረቡን ሲኤንኤን አክሎ ገልጿል።

​በደቡብ ምዕራብ ኢራን በምትገኘው ሎርደጋን ከተማ ተቃዋሚዎች ተሰብስበው የሚታዩባቸውና የተኩስ ድምፅ ከበስተጀርባ የሚሰማባቸው ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጩ ይገኛሉ።

​ ፒቢኤስ እንደዘገበው በዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው ይህ ተቃውሞ በሐሙስ ዕለቱ ወደ ገጠራማ የሀገሪቱ ክፍሎች ተስፋፍቷል።

​ተቃዋሚዎቹ ሰልፍ እየወጡ ያሉት በኢራን እየተባባሰ በመጣው የኢኮኖሚ ሁኔታ ምክንያት ነው። ሲኤንኤን እንደገለጸው ተቃዋሚዎቹ በዋናነት የሀገሪቱ መካከለኛ መደብ ማኅበረሰብ አባላት የሆኑ ነጋዴዎችና ተማሪዎች ናቸው።
​ይህ ተቃውሞ እ.ኤ.አ. በ2022 ማህሳ አሚኒ በኢራን የ ፖሊስ እጅ ከሞተች በኋላ የተቀሰቀሰውን ታላቅ ተቃውሞ ተከትሎ በሀገሪቱ የታየ ትልቁ ተቃውሞ ነው።

ያኔም ተቃውሞው የተጀመረው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ነበር።

​እንደ ፒቢኤስ ዘገባ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን ከተቃዋሚዎቹ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ስለ ሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ማድረግ የሚችሉት ብዙ ነገር እንደሌለ አምነዋል።

​በሀገሪቱ ላይ በተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ምክንያት የኢራን ገንዘብ ዋጋ በእጅጉ ቀንሷል። በተጨማሪም ሀገሪቱ እስራኤልና አሜሪካ የኢራንን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መርሃ ግብር በቦምብ በደበደቡበት የክረምት ወቅት ጦርነት ሳቢያ ከደረሰባት ጉዳት እስካሁን አላገገመችም።
7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.