Logo
YenetaTube
“ግብፅ በታንዛኒያ የገነባችው ግድብ የትብብር ማሳያ ሳይሆን የመከፋፈያ ዘዴ ነው”

- ፈቅ አህመድ ነጋሽ

ግብፅ በታንዛኒያ የገነባችው ግድብ የትብብር ማሳያ ሳይሆን የናይል ተፋሰስ ሀገራትን የመከፋፈያ ዘዴ መሆኑን የቀድሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባልና የውኃ ሀብት ተመራማሪ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ገለጹ።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የታንዛኒያው ጁሌየስ ኔሬሬ የኃይል ማመንጫ ግድብን የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ምሳሌ አድርገው ማንሳታቸውን ተከትሎ ተመራማሪው ለጋዜጣ_ፕላስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ግብፅ ግድቡን የገነባችው እንደማንኛውም ኮንትራክተር ሥራውን ወስዳ እንጂ በነጻ ወይም በትብብር እንዳልሆነ ፈቅ አህመድ ነጋሽ አብራርተዋል።

ግብፅ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል እንዳትሸጥ እንቅፋት ለመሆን እየተንቀሳቀሰች መሆኑንና ለዚህም ለጅቡቲ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ እየገነባች መሆኗን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ግብፅ የታላላቅ ሐይቆች አካባቢ ሀገራት የሚያካሂዱት ልማት ግድቦቻቸው አነስተኛ በመሆናቸው ተጽዕኖ አያደርስብኝም የሚል እምነት ቢኖራትም፣ በምሥራቅ ናይል ላይ ግን አንዲት ጠብታ ውኃ ጥቅም ላይ እንዳይውል ትቃወማለች።

በቅርቡ በናይል የትብብር መድረክ ላይ የታላላቅ ሐይቆችን የልማት ዕቅድ አጽድቃ የምሥራቅ ናይልን ግን አልቀበልም ማለቷን ተመራማሪው አስታውሰዋል።

ግብፅ የምታደርገው እንቅስቃሴ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትን ድጋፍ ለማግኘት ያለመ ቢሆንም፤ ውኃውን በተመለከተ ያላት ተቀባይነት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ተመራማሪው ፈቅ አህመድ ነጋሽ አክለው ገልጸዋል።

@ጋዜጣ_ፕላስ

7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.