Logo
Getu Temesgen
በሲድኒ የሽብር ጥቃት ወቅት ታጣቂውን ትጥቅ ያስፈታው "የቦንዲው ጀግና" አህመድ አል አህመድ የዓለምን ትኩረት ስቧል
#ethiopia | በሲድኒ ቦንዲ ቢች በተካሄደ የሃኑካህ በዓል አከባበር ላይ በታጠቁ ግለሰቦች የተሰነዘረውን አሰቃቂ የሽብር ጥቃት፣ በጀግንነት ተጋፍጦ የብዙዎችን ህይወት የታደገው አህመድ አል አህመድ በመላው ዓለም አድናቆትን እያገኘ ይገኛል። አህመድ በወቅቱ ታጣቂውን በባዶ እጁ በመታገል ትጥቅ ያስፈታ ሲሆን፣ በዚህ ሂደት ላይም በደረሰበት ጥይት ቆስሎ በአሁኑ ወቅት በህክምና ላይ ይገኛል።

የ43 ዓመቱ አህመድ አል አህመድ፣ በሙያው የፍራፍሬ መሸጫ ሱቅ ባለቤት ሲሆን፣ ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በአካባቢው ቡና እየጠጣ ነበር። ታጣቂዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ በከፈቱበት ቅፅበት፣ አህመድ ከጥይቱ ከመሸሽ ይልቅ ወደ አደጋው በመሮጥ አንዱን ታጣቂ ከጀርባው አቅፎ በመያዝ እና ትጥቁን በመንጠቅ ጥቃቱ እንዳይባባስ አድርጓል።

በዚህ እጅግ አስገራሚ የጀግንነት ተግባር ወቅት አህመድ በትከሻው እና በእጁ ላይ ከ4 እስከ 5 የሚደርሱ የጥይት ቁስሎች ደርሰውበታል። የቀዶ ጥገና ህክምና ተደርጎለት አሁን ላይ ነቅቶ በማገገም ላይ የሚገኘው አህመድ፣ ይህንን ያደረገው "ሰዎች ሲሞቱ ማየት ስላልቻለ" እና "ህሊናው ስላላስቻለው" መሆኑን ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።

የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ እና የኒው ሳውዝ ዌልስ ፕሪሚየር ክሪስ ሚንስ አህመድን በሆስፒታል ጎብኝተውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አህመድ "የአውስትራሊያውያን የጀግንነት ተምሳሌት" መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም "በጣም ደፋርና የብዙዎችን ህይወት የታደገ ሰው" ሲሉ አወድሰውታል። ለአህመድ የህክምና እና የቤተሰብ ድጋፍ እንዲሆን የታቀደው የገቢ ማሰባሰቢያ (GoFundMe) በአንድ ቀን ውስጥ ከ1.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማሰባሰብ ችሏል ያለው መናኸሪያ ኤፍ ኤም ነው።

8 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.