Logo
Getu Temesgen
ሲከሰት አደጋ፣ ሲያልፍ የቱሪስት መስህብ የሚሆነው የተፈጥሮ ክስተት
#ethiopia | ዓለማችን እስከ ዛሬ ድረስ በርካታ እና ታላላቅ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎችን አስተናግዳለች። ዛሬም ቢሆን በዓለም ላይ በየቀኑም ሆነ በተለያዩ ጊዜያት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ እና መሰል ጭስ ይከሰታል።

ከሰሞኑ በአፋር ክልል አፍዴራ ወረዳ በሚገኘው የኤርታሌ እሳተ ገሞራ አካባቢ የተከሰተው ፍንዳታ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ከታዩት ፍንዳታዎች የተለየ እንደነበር መገለጹ የሚታወስ ነው።

እንዲህ ዓይነት ፍንዳታዎች ወይም እንቅስቃሴዎች የሚያደርሱት የራሳቸው የሆነ አደጋ መኖሩ ስለማይቀር መጀመሪያ ከአደጋ መራቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊትም ጥብቅ ክትትል እና ምልከታ በማድረግ አደጋውን ቀድሞ ለማወቅ የሚደረገው ጥናት እና ምርምርም በዓለም ላይ ከፍተኛ ነው።

በዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት በፍንዳታው ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ወደ ሌላ ቦታ ለጊዜው ወይም ለዘለቄታው እንዲዘዋወሩ ከማድረግ ጀምሮ ሁሉንም ዓይነት የጥንቃቄ ሥራዎች ይከናወናሉ።

ከዚህኛው በተቃራኒ ደግሞ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች በሁሉም ቦታዎች ሊከሰቱ የማይችሉ በመሆናቸው፤ የሚከሰቱባቸው ቦታዎች ለተመራማሪዎችም ሆነ የተፈጥሮ ሂደቶችን ለመመልከት እና ለመጎብኘት ለሚፈልጉ ሁሉ ትልቅ ዕድል ተደርጎ ይወሰዳል። በተለይ ተጓዥ ቱሪስቶች ለማየት ከሚጓጉላቸው ስፍራዎች መካከል ቀዳሚዎቹ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ያለባቸው ቦታዎች ናቸው።

በዓለም ላይ አብዛኞቹ ተጓዥ ቱሪስቶች የሚጓዙት ተፈጥሮን ለመመልከት እና የተፈጥሮ ክስተቶችን ለማየት እንደመሆኑ፤ ለእነርሱ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ቦታዎች ቅድሚያ ተመራጭ ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2021 በአይስላድ የተከሰተውን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መመልከት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። በወቅቱ በሬይክጃቪክ ተራራ ላይ ተከስቶ የነበረው እሳተ ገሞራ ያስከተለው ጭስ፣ ብናኝ እና አመድ የአየር እና የየብስ ትራንስፖርትን እስከማስተጓጎል ደርሷል።

ክስተቱ በወቅቱ አስደንጋጭ የነበረ ቢሆንም፤ በተቃራኒው ደግሞ ተዳክሞ ለነበረው የአይስላንድ ቱሪዝም ማደግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ከተራራው ላይ የሚፈሰውን የቀለጠ ዓለት ለማየት ቱሪስቶች እስከ ዛሬ ድረስ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ቦታው ይመጣሉ። ይህም የአይስላንድን የቱሪዝም ዘርፍ በእጅጉ ያነቃቃ እና ያሳደገ ሆኗል።

በኢንዶኔዥያ፣ ፔሩ፣ ጃፓን እና ሀዋይ የተከሰቱ የእሳተገሞራ ፍንዳታዎች ያስከተሉት አደጋ ቢኖርም፤ እንደ ጎርፍ፣ አውሎ ንፋስ እና ሌሎቹ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ አደጋ ብቻ አስከትለው አላለፉም።

ከፍንዳታው በኋላ የሚፈጠሩ ለዓይን ማራኪ የሆኑ መልክዓ ምድሮች፣ እንደ ውሃ የሚፈሰው የቀለጠ ዓለት እና በአንድ ቦታ ተከማችቶ የሚታየው የእሳት ባህር የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዙ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎቹ ውጤቶች ናቸው።

እንዲህ ዓይነት ቦታዎችን ለመመልከት ብዙ ተጓዥ ጎብኝዎች ዛሬም ድረስ በየሀገራቱ ይጓዛሉ። ሰዓሊ የሠራው ድንቅ ስዕል የሚመስሉ ፈሰው የደረቁ የዓለት ቅርጾችን መመልከት ከተፈጥሮ አድናቂዎች እስከ ተመራማሪዎች የሚያዘወትሩት ነው።

በእርግጥ የመሬት ውስጥ እንቅስቃሴን በተመለከተ የሚደረጉ ጥናቶች አሁንም ቢሆን የተጠናቀቁ እና የሰው ልጅ ያወቃቸው አልሆኑም። እናም እስከዛሬ ድረስ የመሬት ውስጥ እንቅስቃሴዎችን የሚያጠኑ ባለሙያዎች ሁሉ እሳተ ገሞራ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ አይጠፉም። አንዳንዴም የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሊከሰት እንደሚችል በሚጠበቅባቸው ቦታዎች ላይ ጎብኝዎች እና ተመራማሪዎች በቀጥታ ለመከታተል ቦታው ድረስ ይጓዛሉ።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በአፋር ክልል፣ አፍዴራ ወረዳ፣ ኤርታሌ አካባቢ ኃይሌ ጉብ በሚባለው ቦታ በቅርቡ የፈነዳው አዲስ እሳተ ገሞራ የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ሆኗል።

ከቀይ ባሕር አልፎ እስከ የመን የደረሰው የፍንዳታው ጭስ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ከፍተኛ ሽፋን የተሰጠው ሆኖ ታይቷል።

በ12 ሺህ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደፈነዳ የተነገረለት ይህ እሳተ ገሞራ የፍንዳታው ጭስ ብናኝ በየመን፣ ኦማን፣ ህንድ እና ሰሜናዊ ፓኪስታን መታየቱ ተዘግቧል።

እናም ዕድልን ጭምር ይዞ የሚመጣውን ይህን ክስተት እንደ ሌሎች ሀገራት ሁሉ በማስተዋወቅ በቱሪስት መስህብነት ለመጠቀም መሥራት ይገባል።
#ebc #ethiopia #afar #volcano

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.