Logo
Getu Temesgen
የካይሮ ሰበብ መቆሚያ የለውም
#ethiopia | ሰሞኑን የካይሮ የውሃ ፖለቲከኞች " ኢትዮጵያ ከታላቁ ህዳሴ ሃይል ማመንጫ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ እየለቀቀችብን ነው።" የሚል ወቀሳ እየሰሙ ነው ። በዚህም ለአስዋንና ከዚያ ቀድሞ ለሚገኙ ካናሎች ስጋት እንደሆነባቸው በመገለፅ ጭምር።

የግብፅ የውሀ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ " ሴፕቴምበር 10 ቀን የተለቀቀው የውሀ መጠን 485 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሀ የነበረ ሲሆን ሴፕቴምበር 27 ግን የተለቀቀው ውሀ መጠን 780 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በህዳሴው ግድብ ላይ የሪሞት ሴንሲንግ ጥናት ማድረጉን ያስታወቀው ሚኒስትሩ በዚህም አንድ ሜትር የሚሆን ውሀ መለቀቁን ገልፆ ይህም ከተፈጥሯዊው የአባይ ወንዝ የውሀ ፍሰት ወደ 2 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ የሚሆን ተጨማሪ ውሀ መለቀቀቁን እንደሚያመላክት አስረድቷል፡፡

ከዚህ ቀደም በግድቡ ውሀ ፍሰት ላይ ኢትዮጵያ ተለዋዋጭ እርምጃ መውሰዷን ያስታወቀው መግለጫው በዚህ ወር ደግሞ ማለትም ከኖቬምበር 1 እስከ 20 ከፍተኛ መጠን ያለው ውሀ እንደለቀቀች አስረድቷል፡፡ በተጠቀሱት ቀናት ውስጥ የለቀቀችው ውሀ መጠን በቀን በአማካኝ 180 ሚሊዮን ኪዩብ ሜትር መሆኑን ገልፆም በዚህ ወቅት ከዚህ ቀደም የሚለቀቀው ውሀ 100 ሚሊዮን እንደነበር ጠቅሷል፡፡ በዚህም ልንቆጣጠረው ይገባል የሚል ስሜት አንፀባርቋል።

ትናንት " ግድቡ የውሃ ፍላጎታችንን ያስቀርብናል። " ዛሬ ደግሞ የሚለቀቀው የውሃ መጠን በዛብን ፣ የጎርፍ ስጋትም አሳደረብን።" የሚለው ወቀሳ እርስበርሱ የሚገጭ ትችት ነው ።

ዘላቂ መፍትሄው ግን አገራችን ዋነኛ የውሃው ምንጭ መሆኗን ተቀብሎ ፣ የጋራ ሀብቱ ፍትሃዊና ጤናማ ፍሰት እንዲኖረው ተስማምቶ በጋራ መስራት ብቻ ነው ። ከታሪክ ፀብና ከሴራ አዙሪት ወጥቶ በሰጥቶ መቀበል መኖርም ። የኖረው አካሄድ ግን የተቀየረ ብቻ ሳይሆን ላይመለስ የሞተ ነው።

የቆየው ሴራማ ብዙ ነበር። ከዘፍጥረት ታሪካቸው ጀምሮ የአባይን ውሃ በተመለከተ ግብፆች ሳይጮኹና ሳይሰጉ ያደሩበት አንድም ጊዜ የለም፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ስለአባይ ውሃ ኢትዮጵያን ለማስጠንቀቅ ሙሴ 10ሺ የሚሆን ሠራዊት ይዞ መጥቶ እንደነበር ሰምተናል፡፡

ከዛሬ አንድ ሺ አመታት በፊት የአባይ ውሃ በዝናብ እጥረትና በሌሎች የራሱ ምክንያቶች የውሃ መጠኑ ቀንሶ ስለነበር ‹‹ኢትዮጵያ ገድባው ይሆናል›› በሚል ሥጋት ‹‹አቡነ ሚካኤል›› የተባሉትን ጳጳስ በአማላጅነት ወደኢትዮጵያ ልካ እንደነበርም በኢትዮጵያ በኩል ውሃውን ለመቀነስ በአባይ ላይ የተሰራ አንዳችም የውሃ መቀነሻ ዘዴ አለመኖሩን አረጋግጠው እፎይ ብለውና አመስግነው መመለሳቸውን አንብበናል፡፡

ግብፃዊያን የኢትዮጵያ ህዝብ በእደ-ጥበብና በተግባረ-እድ ሙያ የሰለጠነ እንደሆን፣ አቅም ያገኘ እንደሆን አባይን ከመገደብ አይመለስም በሚል ሥጋት የሞያ እውቀት እንዳይኖረው ባለጅ፣ ቡዳ፣ ቀጥቃጭ… እያሉና የወሩን ቀናት በሙሉ በመላዕክቱና በቅዱሳኑ ስም እየገዘቱ ሥራ እንዳይሰራባቸው በማድረግ ስልጣኔያችንን ወደኋላ ለመጐተት የሰሩት ሴራ ስለመኖሩም በብዙ ታሪኮች ውስጥ አለ፡፡

ኢትዮጵያ በጥንታዊው ታላቅ ስልጣኔዋ ዘመን የአባይን ውሃ ሙሉ ለሙሉ መዝጋት በምትችልበት ዘመን እንኳ ይህን አላደረገችም ፡፡ ኢትዮጵያ በሠራዊት ኃይል ጭምር ከግብጽ እጅጉን የበለጠች በነበረችበት ጊዜ እንኳ ‹‹አባይን ገድቤ የግብጽን ጉሮሮ ልዝጋ›› እንዳላለች ታሪክ ምስክር ነው፡፡

አለቃ ደስታ ተክለወልድ ዘ-ብሔረ ወግዳ ገበታዋርያ በተባለውና በ1928 ዓ.ም. በታተመው መጣፋቸው ገጽ 41 ላይ ይህንኑ የሚያስረግጥ ግጥም አለ፡፡ እንዲህ ይላል፡-

…ያባቶቻችንን ፈረስና ጓዝ
ባህርም አላገደው እንኳን ፈሳሽ ወንዝ
በሰሜን አፍሪቃ ያጤ ዳዊት ጫማ
ሱዳንና ኖባን ሲረግጥ እንደ አውድማ
የግብጽን ጉሮሮ አባይን መዝጋት
በጣታቸው ነበር እንደቀለበት፡፡

ይህ ከጥንት ጀምሮ ያለው የኢትዮጵያ አቋም ዛሬም ቢሆን የተከበረ ነው፡፡ አገራችን ‹‹አባይን ገድቤ የግብጽን ጉሮሮ እዘጋለሁ›› የሚል አቋም ጥንትም አልነበራትም ፣ ዛሬም የላትም፡፡ ታላቁ ግድብ ተጠናቆ እውን የሆነውም በዚሁ ሀቅ ላይ ተመስርቶ ነው።

ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጪያ የሚሆን ኃይል እየሰጠ የሚያልፍ ግድብ ለመስራት አቀደች እውንም ሆነ ፡፡ ለግብጽ የሚሄደው የውሃ መጠን ትርጉም ባለው ሁኔታ ሳይቀንስ/ እላፊ ሳይጨመር ኃይል አመንጭቶ የሚሄድ መሆኑም ይታወቀ ነው ። ውሃ ከተፈጥሮ ጋር ቁርኝት ስላለው የፍሰት መዛባት ቢያጋጥም መፍትሄው መወንጃጀል ሳይሆን በጋራ ችግሩን መፍታት ነው ።

ግብፃዊያን " ኢትዮጵያ የውሃ ምንጫችን ነች ። " ብሎ መንከባከብና መተባበር ብቻ ሳይሆን ልማትና ሰላሟን ማገዝ ላይ ትግተው መስራትም ይኖርባቸዋል ። የግድ!!

( ንጉሥ ወዳጅነው)

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.