Logo
Getu Temesgen
የአትሌቷ ቅጣትና የሪከርዱ ጉዳይ እንዴት ይሆናል?

(ምስጋናው ታደሰ)
#ethiopia | Hydrochlorothiazide (ሀይድሮክሎራይዝድ) HCTZ የተባለ የተከለከለ አበረታች ንጥረ ነገር መጠቀሟ የተረጋገጠባት ኬንያዊቷ የሴቶች ማራቶን የዓለም ሪከርድ ባለቤት ሩት ቼፕንጌቲች የሶስት ዓመታት እገዳ እንደተጣለባት The Athletics Integrity Unit (AIU) ዛሬ (ሐሙስ) ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ገልጬ ፅፌያለሁ።

ይህንን ተከትሎም የሪከርዱ ጉዳይ እንዴት ይሆናል? ለቀድሞዋ የሪከርዱ ባለቤት ትዕግስት አሰፋ ይመለሳል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛሉ።

እናስ?

እናማ ሪከርዱ ወደ ትዕግስት አይመለስም፤ ከሩት ቼፕንጌቲች ጋር ይቆያል።

እንዴት ይህ ሊሆን ቻለ?

የ31 ዓመቷ ኬንያዊት "ሀይድሮክሎራይዝድ" የተባለውን የተከለከለ ንጥረ ነገር መውሰዷ የተረጋገጠባት ማርች 14/2025 በተደረገላት የደምና የሽንት ምርመራ ነው። በመሆኑም ከዛን ጊዜ አንስቶ ጊዜያዊ እገዳ ተጥሎባት የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የሶስት ዓመት እገዳ ተጥሎባታል።

የAIU ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ብሬት ክሎዚዬ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት እገዳው የሚፀናባት ምርመራው ከተደረገላት ከማርች 2025 ወዲህ መሆኑንና ከዛ በፊት የነበሩት ውጤቶቿ የዓለም ሪከርድን ጨምሮ በእጇ እንደሚቆዩ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ስለዚህ ሪከርዱ ወደ ትዕግስት አሰፋ አይመለስም።

ይሁንና ይሄ እስከ መጨረሻው የሚፀና ውሳኔ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ይሄኛው ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ AIU ወደኋላ ተመልሶ በአትሌቷ ላይ ተጨማሪ ምርመራዎችን ጀምሯል።

ለምሳሌ በምርመራው ወቅት ቃለ-ምልልስ ሲደረግላት "ባመመኝ ሰዓት ይሄንን ሀይድሮክሎራይዝድ ጨምሮ ሌሎችንም የባህል መድሃኒቶችን የምትሰጠኝ የቤት ሰራተኛዬ ናት" የሚል ቃል ሰጥታለች። በዚህም ሰራተኛዋም ምርመራ እየተደረገባት ነው።

ቼፕንጌቲች "Rosa Associati" በተባለው የአትሌቲክስ ማኔጅመንት ስር ነው የምትወዳደረው። የዚህ ኩባንያ ባለቤት ጣልያናዊው ፌዴሪኮ ሮሳ (በ2ኛው ፎቶ የሚታየው) ነው።

ይህ ሰው ከ30 በላይ ስመጥር ኬንያውያን አትሌቶችን በስሩ የሚያስተዳድር ሲሆን ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ ለቅጣት ከሚዳረጉት በርካታ የሀገሪቱ አትሌቶች መካከልም አብዛኛዎቹ በእሱ ስር የሚወዳደሩ ናቸው። የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኦገስት 2025 አንስቶ እገዳ ጥሎበታል። ይህንን ተከትሎም እሱም በAIU ምርመራ እየተደረገበት ነው።

ይህም ብቻ ሳይሆን የቼፕንጌቲች የሞባይል ስልክ ላይም ምርመራ እየተደረገ ነው። አትሌቷ መጀመሪያ ላይ ሞባይሏን ላለማስፈተሽ አንገራግራ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ተስማምታለች። ከፌዴሪኮ ሮሳ ጋር የተፃፃፈቻቸው መልዕክቶች እና የመድሃኒት ፎቶዎች እየተመረመሩ ነው።

የእነዚህ ምርመራ ገና በሂደት ላይ ነው። ወደ ኋላ ተሂዶ እየተደረገ ባለው ምርመራና የመጨረሻ ውጤት ከዚህ በፊትም ዶፒንግ ትወስድ እንደነበር ከተረጋገጠባት ሪከርዱን ልትነጠቅና ለትዕግስት አሰፋ ሊመለስላት ይችላል።

8 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.