Logo
Getu Temesgen
ቢል ጌትስ ሮቦቶች ላይ ግብር እንዲጣል ሀሳብ አቀረቡ
#ethiopia | የማይክሮሶፍት ተባባሪ መስራች የሆኑት ቢል ጌትስ፣ ሮቦቶች የሰዎችን ሥራ ሲረከቡ የገቢ ምንጭ የሆኑ ሮቦቶች ላይ ግብር የመጣል ሀሳባቸው አሁን ባለው የቴክኖሎጂ ለውጥ ዘመን ዳግም ትኩረት አግኝቷል።

ይህን ያልተለመደ አስተያየት ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረቡት እ.ኤ.አ. በ2017 ዓ.ም ሲሆን፣ ሀሳቡም ሠራተኞች ላይ ከሚከፈለው የደመወዝ ታክስ ጋር በሚመሳሰል መልኩ፣ ሥራቸውን በሮቦት ለተኩ የንግድ ተቋማት የሮቦት ግብር እንዲጣል የሚያስችል ነው።

በወቅቱ እንደ ረቂቅ አስተያየት የታየው ሀሳብ፣ አሁን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) በምርትና በአገልግሎት ዘርፎች የሰውን ጉልበት በከፍተኛ ፍጥነት እየተካ በመጣበት በዚህ ጊዜ፣ የረዥም ጊዜ አስተዋይነት የታየበት መፍትሔ ሆኖ ቀርቧል።

ምንም እንኳን ጌትስ የሮቦት ግብርን በቀጥታ ከዩኒቨርሳል መሰረታዊ ገቢ (Universal Basic Income – UBI) ጋር ባያያይዙትም፣ እነዚህ ሁለት ጽንሰ-ሐሳቦች የሥራ መጥፋት የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቋቋም በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውይይቶች ላይ ተደጋግመው ይነሳሉ።

ጌትስ በ2017 ባደረጉት አንድ ቃለ ምልልስ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ UBIን ለመቀበል ገና የሚበቃ ሀብት እንደሌላት ገልጸው ነበር። ሆኖም፣ በቅርቡ በ2024 በኔትፍሊክስ ባቀረቡት ተከታታይ ፊልም (What's Next? The Future With Bill Gates) ላይ ያካፈሉት አስተያየት ለውጥ አሳይቷል።

እንደ መናኸሪያ ኤፍ ኤም ዘገባ ከሆነ በድህነት ቅነሳ ላይ ያተኮሩ የUBI ዓይነት ፕሮግራሞች በመጨረሻ የረዥም ጊዜ ወጪ ቁጠባ እንደሚያስገኙ ይከራከራሉ።

ይህንንም ሲያብራሩ፣ በዩናይትድ ስቴትስ የአዋቂዎች ድህነት በዓመት ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስወጣ የሚያመላክተውን መረጃ በመጥቀስ፣ የድህነት ቅነሳ ከጊዜ በኋላ ከሚደረገው ወጪ የበለጠ ጥቅም እንደሚያስገኝ አሳስበዋል።

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.