Logo
YenetaTube
ኒኮላስ ሳርኮዚ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት ከሊቢያ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ተቀብለዋል በሚል ክስ የአምስት አመታት እስር ተፈረደባቸዉ

የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ፤ ከሟቹ የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ በሚሊየን የሚቆጠር ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ በወንጀል ተከሰው የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ከ2007 እስከ 2012 ፈረንሳይን በፕሬዝዳንትነት የመሩት የ70 አመቱ አዛውንት፤ ውሳኔውን ለህግ የበላይነት እጅግ የከበደ ነዉ ሲሉ ገልፀውታል።

በ2007 የምርጫ ዘመቻቸውን ለመደገፍ ከጋዳፊ የተገኘውን ገንዘብ ተጠቅመዋል ተብሎ ክስ የቀረበባቸዉ ሳርኮዚ፤ ጉዳዩ የፖለቲካ ተነሳሽነት ነው ሲሉ ክሱን ውድቅ አድርገዉታል፡፡

በገንዘብ ድጋፉ ምላሽም ፕሬዝዳንቱ፤ በምዕራባውያን ሀገራት እንደ ወንጀለኛ የሚታዩበትን መጥፎ ስም ለመዋጋት ጋዳፊን ለመርዳት ቃል ገብተዋል ሲል አቃቤ ህግ ክስ አቅርቧል።

ሳርኮዚ ለምርጫ ዘመቻው የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የቅርብ ረዳቶቻቸው ከሊቢያ ባለስልጣናት ጋር እንዲገናኙ ፈቅደዋል ተብሏል፡፡

ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ሳርኮዚ የህገወጥ የምርጫ ቅስቀሳ የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚ እንደነበሩ ለማረጋገጥ በቂ ማስረጃ የለም ሲል ቢወስንም የአምስት ዓመት እስራት ፈርዶባቸዋል።

የቀድሞዉ ፕሬዝዳንት ውሳኔውን ይግባኝ ቢሉም ፤ ፍርዱ በእስር ቤት እንዲቆዩ የሚያዝ ነዉ፡፡

በ2012 በድጋሚ ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ሳርኮዚ ለበርካታ የወንጀል ምርመራዎች ኢላማ ሆነዋል።

በ2012 የምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት ከመጠን በላይ ገንዘብ ወጪ በማድረግ እና ይህንንም ለመሸፈን የህዝብ ግንኙነት ድርጅት በመቅጠራቸው ጥፋተኛ ናቸዉ ተብሎ በ2024 የተወሰነባቸዉ ፕሬዝዳንቱ፤ ይግባኝ ጠይቀዉ የአንድ ዓመት እስራቱ ወደ ስድስት ወራት ተቀንሶላቸዉ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በሌላ ክስ ደግሞ በ2014 አንድን ዳኛ ለመደለል ሞክረዋል በሚል ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት የተጣለባቸዉ የመጀመሪያው የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት በመሆን እስራት ተፈርዶባቸዉ ነበር እንደ ቢቢሲ ዘገባ፡፡

Via Ethio fm

11 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.