Logo
Getu Temesgen
አራት ሺህ ለሚልቁ ወጣቶች እንጀራ ማግኘት ሰበብ የሆነችው እንስት
#ethiopia | ሜላት ንጉሴ ትባላለች። ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ እናት ናት። ትውልዷ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ነው።

ዕድገቷ ደግሞ ቦረና እና አዲስ አበባ። ቦረና ከሴት አያቷ ዘንድ አድጋለች። ከአያቷ ማደጓና ከእርሳቸው የወረሰቻቸው በጎ ባህሪያት ከመልካም ስራዎች ጋር እንዳቆራኛት ትናገራለች።

ሜላት ማህበራዊ ሚዲያን በወጉ የምትጠቀም እንስት ናት። በፌስቡክ ላይ 185 ሺህ ተከታዮች አሏት። ያላትን ተሰሚነት በመጠቀም የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትን ትከውናለች።

ክረምትና በጋ ሳትል ለመልካም ነገር ሳትቦዝን ትለፋለች። የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሠው ሠራሽ ችግሮች ሲደርሱ አለሁ ባይ ናት።

በተስፋ አዲስ የካንሰር ህሙማን ማዕከል ውስጥ በርካታ መልካም ተግባራትን ከውናለች። ለአካል ጉዳተኞች ዊልቼር አሰብስባ ሰጥታለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሌላ በጎ ምግባር ተከስታለች።

ይህም የማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ስራ ፈላጊና አሰሪን የማገናኘት ተግባር ነው። ለዚህ ስራ ምንም አይነት ክፍያ አትጠይቅም። ይህን ለማድረጓም መነሻ ምክንያት ነበራት።

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስራ በማጣት ራሱን ያጠፋ ልጅ ነበር መነሳሳት የሠጣት። በአንድ ሰው ምክንያት የተጀመረው የሜላት በጎ ስራ ከአራት ሺህ ለሚልቁ ጉሮሮዎች እንጀራ ማቀበል ችሏል። በእሷ ምክንያት ከአራት ሺህ በላይ ዜጎች ስራ ማግኘት ችለዋል።

ለዚህና ሌሎችም መልካም ተግባሮቿ በርካታ እውቅናና ሽልማቶች ተሠጥተዋታል። ሰሞኑንም ትልልቅ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች እና ባለስልጣናት እጩ በተደረጉበት የስታር ዋይድ አዋርድ (star wide award) ላይ አሸንፋ ተሸልማለች።

"ለሶሻል ሚድያ ጊዜ መስጠታችን ካልቀረ ለበጎ እናውለው ብንል ይኸው እውቅና እያሰጠን ይገኛል።" ስትልም ስሜቷን ገልፃለች።

በመልዕክቷም "ይሄ ሽልማት የኔ ብቻ አይደለም፤ የምታበረታቱኝ ወዳጅ ቤተሰቦቼ ውጤት ነው። ልትኮሩ ይገባል" ብላለች።

በዳግማዊት ግርማ
#gazette_plus

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.