Logo
Getu Temesgen
ኪም ጆንግ ኡን፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ሌሎችመሪዎች በቻይና የመከላከያ በዓል ላይ ሊገኙ ነው
#ethiopia | የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሚቀጥለው ሳምንት በቤጂንግ በሚካሄደው የመከላከያ ትርኢት በዓል ላይ እንደሚታደሙ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ይህም ኪም ጆንግ ኡን የሚያደርጉት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የመሪዎች ግንኙነት እንደሆነ ታምኗል።
"የድል ቀን" እየተባለ የሚጠራው የቻይና የመከላከያ ትርኢት በዓል ከጃፓን ጋር ያደረገችው ጦርነት እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት 80ኛ ዓመት መታሰቢያ ነው።

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበዓሉ ላይ ይታደማሉ ከተባሉ የ26 አገራት መሪዎች ውስጥ አንዱ ናቸው።
መሪዎቹ የሚሰባሰቡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኪም ጆንግ ኡንን ለማግኘት እንደሚሹ ባሳወቁ በቀናት ውስጥ ነው።

ቻይና በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር አውሮፕላኖችን፣ ታንኮችን እንደሁም የፀረ ድሮን ስርዓቷን ጨምሮ የታጠቀቻቸውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች በበዓሉ ላይ ታሳያለች።

በመከላከያ በዓሉ የቻይና ጦር ሠራዊት አባላት እና ጡረታ የወጡ ወታደሮችን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ከቲያንመን አደባባይ ተሰልፈው ትርኢት ያሳያሉ ተብሏል።

ለ70 ደቂቃ የሚቆየው ወታደራዊ ትርኢት በተንታኞች እና በምዕራቡ ዓለም ጥብቅ ክትትል የሚደረግበት እንደሆነ ይጠበቃል።

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ የቤጂንግን የቅርብ አጋር ፒዮንግያንግን አስርት ዓመታትን ለዘለቀው ወዳጅነታቸው ያሞገሰ ሲሆን፤ ሁለቱ አገራት "ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት" መተባበራቸው ይቀጥላሉ ብሏል።

የኪም ጆንግ ኡን በበዓሉ መታደም ትልቅ አንድምታ ያለው ሲሆን፤ እ.አ.አ በ2015 በተደረገው የቻይና የድል ቀን ፒዮንግያንግ ከፍተኛ ሹሟን ቾ ሪዮንግ-ሂን ልካ የነበረ መሆኑን ኢትዮ ኤፍ ኤም ቢቢሲን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

12 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.