Logo
FastMereja
ወደ ውጭ ሀገር እልካለሁ በማለት ከተለያዩ ግለሰቦች ከ1.3 ሚሊየን ብር በላይ አጭበርብሮ የተሰወረን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
***
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 08 ቀን 2017 ዓ/ም (አዲስ ፖሊስ)፦ ጌትነት እንዳሻው የተባለ ተከሳሽ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው መገናኛ ሠላም ታወር ህንፃ ላይ ቢሮ ተከራይቶ ‹‹ ኤልያና የጉዞና አማካሪ ድርጅት ›› የሚል ህጋዊ እውቅና የሌለው ድርጅት በመክፈት ሰዎችን ወደ ውጭ ሀገር እልካለሁ በሚል ከተለያዩ ግለሰቦች እስከ 1 ሚሊየን 360ሺህ ብር ድረስ በመቀበል የማጭበርበር ወንጀል ሲፈፅም እንደነበረ ፖሊስ ገልጿል።

ግለሰቡ ግንቦት 09 ቀን 2017 ዓ/ም የግል ተበዳይ ብርቱካን እመብርሀን የተባለች ግለሰብን ወደ ውጭ ሀገር እልክሻለሁ በማለት 340ሺህ ብር በመቀበልና ቼክ እንደማታለያ በመስጠት ግለሰቧንም በተባለው ቀን ወደ ውጪ ሊልክ ባለመቻሉ ለፖሊስ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

ከግለሰቧ ክስ በተጨማሪም ሰናይት ተክላይ፣ ሠናይት ገ/ኪዳን እና አብረኀት የተባሉ ግለሰቦች ከእያንዳቸው 340ሺህ ብር በመቀበልና ወደ ውጪ ሀገር እልካችኋለሁ በማለት መሰወሩን በመግለፅ ተጨማሪ ሪፖርት ለፖሊስም ደርሶታል፡፡

የክ/ከተማው ፖሊስ የቀረበለትን ክስ መሰረት በማድረግ ባደረገው መረጃ የማሰባሰብ ተግባር ተጠርጣሪው ዜጎችን ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ምንም ዓይነት ህጋዊ ፈቃድ የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ በተለያዩ ክ/ከተሞች በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ክስ ተመስርቶበት እየተፈለገ እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል፡፡

ግለሰቡን ሲፈለግና ሲያፈላለግ የነበረው ፖሊስም ነሐሴ 07 ቀን 2017 ዓ/ም ባደረገው ብርቱ ክትትል ተከሳሽ ይኖርበታል በተባለው ለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ቦታው የካ አባዶ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከጠዋት 12፡00 ሠዓት ላይ በቁጥጥር ስር ሊውልም ችሏል፡፡

ፖሊስ በግለሰቡ ላይ ተጨማሪ ምርመራ የማስፋት ተግባሩን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከዚህ ቀደም በዚህ ግለሰብ ተመሳሳይ የማጭበርበር ወንጀል ተፈፅሞብኛል የሚል አካል ካለም የካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በአካል በመቅረብ መረጃ መስጠት የሚችል መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ወደ ውጭ ሀገር እንልካለን የሚሉ አንዳንድ አካላት ተግባራቸው ህጋዊነትን የተከተለ መሆኑን በሚገባ ማረጋገጥ ለመሰል የወንጀል ድርጊቶች ተጋላጭ ከመሆን ያድናል ሲልም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.