Logo
EBC
የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ያከሸፈው የኢትዮጵያ ፅናት
**************

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፕሮጀክቱ በአለም አቀፍና በቀጣናዊ መድረኮች በርካታ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች ሲያጋጥሙት ቆይተዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የልማት መብት ለመገደብ የተደረጉ ሴራዎችም ብዙ ርቀት የተጓዙ ቢሆንም ኢትዮጵያ እነዚህን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች በፅናት በመቋቋም የግድቡን ግንባታ በተሳካ ሁኔታ አጠናቃ ለውጤት አብቅታለች።

ዛሬ ላይ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሀገራችን የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ከፍታ ማሳያ ከመሆኑም በላይ ከረጅም ዘመናት የባህር በር ማጣት ጋር ተያይዞ ለተነሳው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ቁልፍ የታሪክ ምእራፍ ሆኗል።

ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ለመቀልበስ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። ጉዳዩን የአረብ ብሄራዊ ደህንነት ስጋት በማስመሰል የአረብ ሊግ አባላት በኢትዮጵያ ላይ ወጥ አቋም እንዲይዙና ዲፕሎማሲያዊ ማእቀብ እንዲጥሉ ከመጎተቷም ባሻገር የግድቡ መሰራት በታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ከባድ የውሃ እጥረት እንደሚፈጥር በማስመሰል መጠነ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን አካሂዳለች።

ከአስመራ እስከ ካይሮ ባሉት ሀይሎች የሚመራውና የሚደገፈው ይህ የጥፋት መረብ በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍንና በምጣኔ ሀብት እንዳትለማ ለማደናቀፍ እንዲሁም አልፎ አልፎ የሚነሱ የፖለቲካ አለመግባባቶችን በመጠቀም የሀገራችንን የድርድር አቅም ለማዳከም ጥረት አድርጓል።

ሆኖም ኢትዮጵያ በህዝቧ ሁለንተናዊ ድጋፍና በፅናት ፍትሃዊ እና ተመጣጣኝ የውሃ አጠቃቀም የሚለውን መርህ አፀንታ በመያዝ የናይል ተፋሰስ ሀገራትን የትብብር ማእቀፍ ስምምነት አፅድቃለች።

ይህ በዓባይ ላይ የተመዘገበው ታሪካዊ ድልና እያደገ የመጣው የኢኮኖሚ አቅም ኢትዮጵያ በቀይ ባህር የሚገባትን ስፍራ ለማግኘት የምታደርገውን የመደራደር አቅምን በማሳደግ በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፋል።

ኢትዮጵያ ከጥንቱ የአክሱም ስልጣኔ እስከ አዱሊስ ወደብ ድረስ የባህር በር ባለቤት የነበረች ሲሆን ዛሬም ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ያላት ሀገር በመሆኗ የባህር በር ማግኘት የህልውናና የልማት ጥያቄ እንጂ ሌላን ሀገር ለመውረር የሚደረግ ጉዞ አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለፁት ኢትዮጵያ በታሪክም ሆነ በዓለም ህግ መሰረት በሰላማዊ መንገድ የባህር በር የማግኘት መብት ስላላት የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና አትኖርም።

ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ በራሷ አንጡራ ሀብትና አቅም ገነብታ የቀጠናው የልማትና የእድገት ማእከል እንዳደረገችው ሁሉ የቀይ ባህር መዳረሻ ፍላጎቷንም ቢሆን ሌሎችን ባገለለ መልኩ ሳይሆን በሰላም፣ በህግ፣ በዲፕሎማሲና በህዝቦቿ የተባበረ ብርታት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርታ እውን ታደርጋለች።

በብሌን ደምበሎ
#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ
#ethiopiandiplomacy #sovereignty #ethiopianpanafricanism #geopolitics #hornofafrica

1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.