Logo
EBC
የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ የፈጠረው ግዙፍ አቅም
**********************

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ወቅት የተናገሩት "ከሕዳሴ ግድብ በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ እና ከግድቡ በኋላ የምትኖረው ኢትዮጵያ አንድ አይደሉም" የሚለው ንግግር ዛሬ በተግባራዊ እውነታነት የተረጋገጠ ብሔራዊ መገለጫ ሆኗል።

በዜጎቿ የተቀናጀ ዕውቀት እና ጥረት የተጠናቀቀው ይህ ታላቅ ግድብ ለዘመናት ተጭኖብን የነበረውን የዕርዳታ እና ጥገኝነት አስተሳሰብ በመስበር ኢትዮጵያ በራሷ ብቃት እና አቅም መቆም እንደምትችል ለዓለም ያሳየችበት ታላቅ ድል ነው።

ግድቡ ከ5 ሺህ 150 ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የውስጥ አቅርቦትን ከ50 በመቶ በላይ ከመሸፈኑ ባሻገር፣ ለጎረቤት ሀገራት የኃይል አቅርቦት በመዘርጋት ኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ የኢነርጂ ማዕከል አድርጓታል።

የሕዳሴው ግድብ ፍጻሜ የኃይል ማመንጫ ተቋም ከመሆን ባለፈ ባለፉት አምስት ዓመታት የደረጀውን አዲስ እና ፈጣን የፕሮጀክት ትግበራ አቅም ያበሰረ የመንደርደሪያ ምዕራፍ ነው።

እነሆ ከሕዳሴው በኋላ ያለችው ኢትዮጵያ ግዙፍ እና ፈጣን አቅም የገነባች መሆኗን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

ቀደም ሲል 5 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ለመገንባት ከዐሥር ዓመታት በላይ ስትታገል የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ በፈጠረችው ከፍተኛ የአሠራር ቅልጥፍና እና ብሔራዊ የፋይናንስ አቅም በአንድ ጊዜ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጁ አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የመተግበር ግዙፍ ከፍታ ላይ ደርሳለች።

ይኸውም ከ5 ቢሊዮን ዶላር ነጠላ ፕሮጀክት ትግበራ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የብዙ ፕሮጀክቶች አስተዳደር የተደረገ የስድስት እጥፍ አቅም ዕድገት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማሳያ ነው።

በግድቡ ምረቃ ዕለት በጉባ የተበሰሩት እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ፣ አቪዬሽን እና ማኅበራዊ ልማት ከመሠረቱ የሚቀይሩ ናቸው።

ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለውና የኢትዮጵያ አየር መንገድን አህጉራዊ መሪነት የሚያጸናው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጥናት፣ እንዲሁም የነዳጅ ገቢ ምርት ወጪን በማስቀረት የኢነርጂ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጡት የተፈጥሮ ጋዝ እና የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች የዚሁ ግዙፍ አቅም ውጤቶች ናቸው።

በተጨማሪም የግብርናውን ዘርፍ ከውጭ ጥገኝነት ነፃ የሚያወጣው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው እየተፋጠነ ነው። በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሚገነቡት 1.5 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች የዜጎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራሉ።

ከእነዚህ የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች ባሻገር፣ በአዲስ አበባ ተጀምሮ ወደ 75 በላይ ከተሞች የተስፋፋው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ምርታማነት እና የሎጂስቲክስ ቅልጥፍና በከፍተኛ ደረጃ ቀይሮታል።

የወልመል፣ የጎዴ እና የቄጦ የመስኖ ግድቦች መጠናቀቅ፣ የገጠር ሞዴል መንደሮች ልማት እና አርሶ አደሩን ሀብት አስይዞ ብድር የሚያገኝበት የግብርና ፋይናንስ ፍኖተ-ካርታ መዘርጋቱ የዚሁ ሁለንተናዊ አቅም አካላት ናቸው።

ከሕዳሴው ግድብ ማጠናቀቅ በኋላ ኢትዮጵያ ያዳበረችው አቅም የኃይል አቅርቦትን ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ብሔራዊ የራስ መተማመንን፣ ግዙፍ የፋይናንስ እንቅስቃሴን እና የሜጋ ፕሮጀክቶች ትግበራ ጥበብን ያካተተ ነው።

በአሁኑ ወቅት የተጀመሩት የ30 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶች እና የኮሪደር ልማቶች አዲሷ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የሎጂስቲክስ የበላይነቷን በማያወላውል መሠረት ላይ እየገነባች መሆኗን የሚያረጋግጡ ሕያው ምስክሮች ናቸው።

በለሚ ታደሰ
#ethiopia #ebc #gerd #megaprojects #development #africa #infrastructure

22 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.