Logo
EBC
የባሕር በር ጥያቄያችን ታሪካዊ መብት፣ የኢኮኖሚ ኅልውና እና ይህ ትውልድ በቁርጠኝነት የሚያሳካው ሀገራዊ ህልም
*************************

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ በሕዝብ ብዛት፣ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና በጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂካዊ ስፍራዋ ከፍተኛ ሚና የምትጫወት ታላቅ ሀገር መሆኗ የዓለም እውነት ነው። ቢሆንም ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የባሕር በር አልባ ሆና ቆይታለች።

ይሁን እንጂ የባሕር በር ማግኘት ለአንድ ሀገር የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የብሔራዊ ጥቅም፣ የኢኮኖሚ ኅልውና እና የረጅም ጊዜ የደኅንነት መሠረት በመሆኑ፣ ይህ ታሪካዊ ፍላጎት በዓለም አቀፍ ሕግና በሰላማዊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በዚህ ትውልድ ቁርጠኝነትና የጋራ ትግል በብቃት እውን እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለ።

በአሁኑ ወቅት ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣ የገቢና ወጪ ንግዷን በጎረቤት ሀገራት ወደቦች በኩል ብቻ የምታከናውን በመሆኗ ለወደብ አገልግሎት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንድታወጣ ተገዳለች።

የሕዝቧ ቁጥር በፈጣን ሁኔታ እየጨመረ እና የኢንዱስትሪ ዘርፏ እየሰፋ በመጣበት በዚህ ዘመን፣ የቀጥታ የባሕር በር ማግኘት የሎጂስቲክስ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ የሀገራችን የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል።

በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የሚታዩት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነት በቀጥታ የሚነኩ በመሆናቸው፣ አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት ለቀጣናዊ ደኅንነቷ እና ለባሕር ላይ ንግድ መስመሮች ጥበቃ ወሳኝ ነው።

አንድ ግዙፍ ሕዝብና ኢኮኖሚ ያላት ሀገር የባሕር በር እና የባሕር ኃይል አልባ ሆና እንድትቀጥል ማድረግ የጂኦ-ፖለቲካ ሚዛኑን የሚያሳጣ በመሆኑ፣ የባሕር በር ጥያቄያችንን ማሳካት የሰላምና የመረጋጋት ዋስትናችን ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት በመጣስ የሚከናወን ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ሕጎች፣ በሰላማዊ ዲፕሎማሲ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ ነው።

የባሕር ሀብትን በጋራ የመጠቀም፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን የማቀናጀት እና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት የመፍጠር አቀራረባችን ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።

የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ወሳኝ የሆነ የብሔራዊ ጥቅም ማዕከል በመሆኑ፣ ይህ ትውልድ በበሰለ ዲፕሎማሲ፣ በጽኑ ሀገራዊ አንድነትና በስትራቴጂካዊ እይታ ይህንን ህጋዊ እና ታሪካዊ ፍላጎት በድል በማጠናቀቅ የሀገሩን ልዕልና ዳግም ያረጋግጣል።

ይህ ትውልድ የቆየውን ታሪካዊ ስብራት ጠግኖ፣ የቀጣናውን ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት በማሳመንና በቁርጠኝነት በመታገል የኢትዮጵያን የባሕር በር ህልም እውን እንደሚያደርገው ምንም ጥርጥር የለውም።

በአድማሱ አራጋው
#ethiopia #ebc #ethiopiaseaoutlet #redseadiplomacy #nationalinterest #hornofafricaintegration #ethiopiansovereignty

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.