Logo
Getu Temesgen
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለባቡልኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
#ethiopia | ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በትላንትናው ዕለት ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ለባቡልኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት የ2 ሚሊዮን ብር እና የአልባሳት ድጋፍ አደረገ። ይህ ድጋፍ የባቡልኸይርን ሰብዓዊ አገልግሎቶች ለማጠናከር ያለመ መሆኑን በመርሐግብሩ ላይ ተገልጿል።

በድጋፍ ፕሮግራሙ ላይ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዊም ቫንሄለፑት፣ የውጭ ግንኙነት ዋና ኃላፊ ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ እና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሠራተኞች ተገኝተው የድርጅቱን ማዕከል ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ የምሳ ግብዣ የተደረገ ሲሆን፣ ባቡልኸይር በማዕከሉ ከሚረዳቸው በተጨማሪ ቤት ለቤት የሚረዳቸውን ወገኖችም ጠይቀዋል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዊም ቫንሄለፑት ባስተላለፉት መልእክት፣ ይህ የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪም በሠራተኞች የተሰበሰቡ አልባሳት አስረክበዋል።

አቶ ቫንሄለፑት፣ መላው ኢትዮጵያውያን ባቡልኸይርን በኤም ፔሳ አፕሊኬሽን አማካኝነት በቀላሉ መደገፍ የሚያስችል መንገድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ይህንንም ለማስጀመር፣ ለ10 ሚሊዮን ደንበኞቻቸው ለአንድ ዓመት የሚቆይ የአጭር መልእክት ዘመቻ ዕድል መሰጠቱን እና እሳቸውም በግላቸው 50 ሺህ ብር በማስገባት ዘመቻውን ማስጀመራቸውን ገልጸዋል።

ባቡልኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት በጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በመዝገብ ቁጥር 4513 ተመዝግቦ በሴቶች ብቻ የተቋቋመ ሰብዓዊ ድርጅት ነው።

ላለፉት አምስት ዓመታት ድርጅቱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ የቆየ ሲሆን፣ በተለይም ከ5,000 በላይ ቤተሰቦች በቀን ሁለት ጊዜ ጤናማ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ የምሳና የእራት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ለበርካታ ቤተሰቦች የጤና መድን አገልግሎት እያቀረበ ነው።

ድርጅቱ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሴቶችና እናቶች ቋሚ የሥራ ዕድሎችን የፈጠረ ሲሆን፣ በርካታ ወጣቶችንና ሴቶችን እንደ ልብስ ስፌት፣ ኮምፒዩተር እና ጫማ ሥራ ባሉ የሙያ ስልጠናዎች በማሰልጠንና በማስመረቅ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው መተዳደሪያ እንዲያገኙ አስችሏል።

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.