Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) አውሮፓ በከባድ የሙቀት ማእበል ውስጥ ወደቀች፡፡ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ውስጥ የሙቀት መጠኑ ከ40 ዲግሪ ሰልሺየስ ወይንም ከ104 ዲግሪ ፋራናይት በላይ እየሆነ መምጣቱን ኤኤፍፒ ዛሬ ባቀረበው ዘገባ ገልጿል፡፡ ይህም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የጤና ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት እንዳደረሳቸው አስታውቋል፡፡ ሳይንቲስቶችና ባለስልጣናት እንዲህ አይነት ከባድ የሙቀት ማእበሎች እየተደጋገሙና እየተለመዱ መምጣታቸውን በመግለፅ ላይ መሆናቸውን የጠቀሰው ዘገባው ይህ ማእበል በማህበረሰብ ጤና ስርአቶች፣ በሀይል ማመንጫዎች፣ በትራንስፖርት ኔትወርኮችና በቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ላይ ተፅእኖ መፍጠሩን አስረድቷል፡፡

ከእነዚህ አገራት መካከል በቀዳሚነት የጠቀሰው ጣሊያንን ሲሆን በዚህ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና ዋና ከተሞች የጤና ማስጠንቀቂያ አዋጅ መተላለፉን አስረድቷል፡፡ የጣሊያን ጤና ሚኒስትር ትላንት ባወጣው መግለጫ በ27 ከተሞች ውስጥ ከፍተኛ ሙቀት መከሰቱ መመዝገቡን ገልፆ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ይህ ማስጠንቀቂያ እንደወትሮው አረጋዊያንንና ስር የሰደደ ህመም ያለባቸውን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ በማስጠንቀቂያው ሁሉም ነዋሪዎችና ቱሪስቶች ከፍተኛ ሙቀት በሚከሰትበት ወቅት ከፀሀይ ቀጥተኛ ብርሀን እንዲቆጠቡና በተቻለ መጠን ቤት ውስጥ በመቆየት ብዙ ውሀ እንዲጠጡ አሳስቧል፡፡ የተከሰተው ሙቀት በቱሪስት መስህቦች ጉብኝት ላይ ማስተካከያዎች እንዲረጉም ያስገደደ ነው፡፡

የጣሊያን ቱሪዝምና ባህል ቢሮ የሮም ኮሎሲምና ፓንቴዎንን ጨምሮ የትልልቅ መስህቦች በሮች በምሽት እንዲከፈቱ ትእዛዝ ማስተላለፉን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ እንደዘገባው ኦስትሪያና ስሎቫኪያ ብሄራዊ የሙቀት ሪከርዳቸውን ሰብረዋል፡፡ ትላንት ሀሙስ በስሎቫኪያ ደቡባዊ ክፍል 42.2 ዲግሪ ሰልሺየስ ሙቀት መከሰቱን የአገሪቱ ሜትሮሎጂ ያረጋገጠ ሲሆን ይህም በአገሪቱ ውስጥ ከተፈጠረው ሙቀት ትልቁ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህች አገር በጋብቺኮቮ የሚገኘው ትልቁ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ በውሀ እጥረት የተነሳ ከስምንቱ ተርባይኖች ሰባቱን መዝጋቱም ተዘግቧል፡፡

በኦስትሪያም ሮብ እለት 41.2 ዲግሪ ሰልሺየስ የሆነ በአገሪቱ ታሪክ ትልቁ የሚባል ሙቀት እንደነበረ ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በሀንጋሪ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ድርቅ የዳኑቢ ወንዝን የውሀ መጠን በመቀነሱ በአገሪቱ ብቸኛ የሆነው የኒውክሌይር ሀይል ማመንጫ ላይ ተፅእኖ አሳድሯል፡፡ እንደዘገባው ይህ ሀይል ማመንጫ ማብላያዎቹን ለማቀዝቀዝ የሚጠቀመው የዚህን ወንዝ ውሀ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ መንግስት የሀይል ቁጠባን በግዳጅ ማስተዋቅ የጀመረ ሲሆን ከቀኑ 5 ሰአት እስከ ምሽቱ 10 ባለው ጊዜ ኢንዱስትሪዎችና ቤተሰቦች የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ የጭነት ባቡሮች በእነዚህ ሰአታት አገልግሎት እንዳይሰጡም ታግደዋል፡፡

ቡዳፔስት የምታትወቅበት የምሽት ላይ የሚያብለጨልጩ መብራቶችም እንዲጠፉ ተደርገዋል፡፡ በጀርመንም ቢሆን በራይንና በሌሎችም ወንዞች እየተከሰተ ያለው የውሀ መጠን መቀነስ በትራንስፖርትና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ተፅእኖ እያሳደረ ነው፡፡ በፈረንሳይ የተከሰተው ሰደድ እሳትም የዚሁ የሙቀት መጨመሩ ተፅእኖ እንደሚገኝበት ዘገባው ገልጿል፡፡ ጁላይ 20 የጀመረው ሰደድ እሳት ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ላይ ቃጠሎ መፍጠሩን ጠቅሶ ይህም ከቅርብ አስርታት ወዲህ በአገሪቱ ከተከሰቱ ትልልቅ ሰደድ እሳቶች አንዱ ሆኖ እንዳስመዘገበው አስረድቷል፡፡ ከአውሮፓ ውስጥ ቀዝቀዝ ያለ ሙቀት ያለው በእንግሊዝ ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባለፈው ወር በነበረው ከፍተኛ ሙቀት የደረቁት ሳሮች ላይ ትላንት በተነሳው ቃጠሎ የተነሳ የሂዝሮው አየር ማረፊያ ደቡባዊ አውሮፕላን ማኮብኮቢያ ለጊዜውም ቢሆን እንዲዘጋ አስገድዶ እንደነበር ዘገባው ጠቅሷል፡፡

20 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.