Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) የክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሰርግ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶና ጆርጂና ሮድሪጌዝ በዚህ ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ጋብቻቸውን እንደሚያከናውኑ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ለ10 አመታት ያህል አብረው የኖሩት ጥንዶቹ 5 ልጆችን እያሳደጉ ቢሆንም የሰርጋቸውን በአል የሮናልዶ የትውልድ ስፍራ በሆነችው ደሴት ለማድረግ መምረጣቸው ተነግሯል፡፡ የሰርጉ ስነስርአት በፈንቻል በሚገኘው ባለ5 ኮከቡ ሳቮይ ፓላስ ሆቴል ውስጥ እንደሚከናወን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡

እንደዘገባው ከሆቴሉ ዝግጅት በፊት ሙሽሪት በማዴይራ ደሴት ዋና ከተማ ፈንቻል በሚገኘው ካቴድራል ውስጥ ቬሎዋን ለብሳ በህዝብ መሀል ትራመዳለች፡፡ ካቴድራሉ 800 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው ነው፡፡ በዚህ ካቴድራል ሀይማኖታዊው የጋብቻ ስነስርአት ከተደረገ በኋላ ሙሽሮቹ ከካቴድራሉ በመኪና አምስት ደቂቃ ወይንም በእግር 15 ደቂቃ ወደሚርቀው ባለ5 ኮከቡ የቅንጦት ሆቴል እንደሚጓዙ ዘገባው አስረድቷል፡፡

ሙሽሮቹ በዚህ ሆቴል የላይኛው ክፍል በሚገኘው ‹‹ዘ ሪዘርቭ›› ወይንም በሆቴል ውስጥ ሌላ ሆቴል ውስጥ ቆይታ እንደሚኖራቸው የጠቀሰው ዘገባው ይህ ቦታ ለቤተሰቡ ምቹ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡ የራሱ ጃካራንዳ ላውንጅ፣ ትልቅ መዋኛ ገንዳ፣ የግል መመገቢያና የግል አስተናጋጆች ላሉት ለዚህ ክፍል የአንድ ቀን መቆያ ዋጋው 1100 ፓውንድ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው የሰርግ ስነስርአቱ በዚህ ሆቴል ምሽት ላይ በሚከናወን የእራት ግብዣ እንደሚጠናቀቅ ገልጿል፡፡ ከሆቴሉ የቅንጦት ቦታዎች አንዱ በሆነው ትልቁ አዳራሽ ውስጥ 1000 ያህል እንግዶች እንደሚታደሙም አስረድቷል፡፡

ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ ይህንንና መሰል የሰርጉን ዝርዝሮች ለንባብ ያበቃ ቢሆንም ጉዳዩን አነጋጋሪ ያደረገው ጥንዶቹ ስለሰርጉ ምንም ማረጋገጫ ያልሰጡ መሆናቸው ነው፡፡ እንዲሁም የሮናልዶ እህቶች የሆኑት ካቲያና ኤልማ ጥንዶቹ በዚህ አመት ሰርጉን እንደማያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ጋብቻው ይደረግበታል የተባለው ካቴድራልም ቅዳሜም ሆነ እሁድ በሮናልዶና ሮድሪጌዝ ስም የተመዘገበ የጋብቻ ቀጠሮ እንዳልያዘ ገልጿል፡፡

13 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.