Logo
YenetaTube
በፊንቴክ ኢንቨስትመንት ማጭበርበር የተጠረጠሩ አርቲስቶች ላይ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው አቤቱታ ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት ቀጠሮ ተሰጠ።

በ"ፊንቴክ" ኢንቨስትመንት ሽፋን በተፈጸመ መጠነ ሰፊ የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ታዋቂ አርቲስቶች፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ሐምሌ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።

ነገር ግን ተከሳሾቹ "እግረኛው" በተሰኘ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ቀርበው መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ፣ ዐቃቤ ሕግ ባለ 5 ገጽ የክስ አቤቱታ አቅርቦ ስለነበር ጉዳዩ ከሰዓት በኋላ በሌላ ችሎት እንዲታይ ተደርጎ ፣ ለዛሬ ነሐሴ 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ጠዋት 4፡00 ሰዓት ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

ጠዋት በነበረው ችሎት ጋዜጠኛ ተክለሃይማኖት አዳነን ጨምሮ አርቲስቶቹ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ዐቃቤ ሕግ ላቀረበው አቤቱታ በጽሑፍ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም በሕግ በተያዘ ጉዳይ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ለምን መግለጫ እንደሰጡ የቃል ማብራሪያ አቅርበዋል።

ተከሳሾቹ በሰጡት ምላሽ፦ "እኛ የኪነ ጥበብ ሰዎች ነን፤ ነገር ግን በመልካም ስማችን ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ስለተከፈተብንና ስማችን በመጥፋቱ ሥራችን ስለተበላሸ ነው ምላሽ ለመስጠት የተገደድነው" ብለዋል።

"ለምሳሌ በዚህ ምክንያት አምስት የሥራ ውሎች ተቋርጠውብኛል፤ እኔና ጓደኛዬ የምንሰራው የቴሌቪዥን ፕሮግራምም እንዲቋረጥ ተደርጓል" ሲል አርቲስት ይገረም ደጀኔ ለችሎቱ አብራርቷል።

በነበረው መግለጫ የፍርድ ቤቱን የሕግ ሂደት እንዳያስተጓጉሉ ጥንቃቄ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
አርቲስቶቹን በማኅበራዊ ሚዲያ አናግሮ መግለጫቸውን ያስተላለፈው ጋዜጠኛ ተክለሃይማኖት አዳነ በበኩሉ፦ "እኔ ይህን ፕሮግራም ሳቀርብ የመጀመሪያዬ አይደለም፤ አርቲስቶቹ በሕግ ከመያዛቸው አስቀድሞ አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬን በፊንቴክ ዙሪያ ተገልጋዮች ስለሚያነሱት ቅሬታ ጠይቄ ሰርቻለሁ፤ ከዚያ በኋላም አርቲስቶቹን ጥፋተኛ አድርገው በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚዘግቡትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ የጠየቅኋቸው ሰዎች አሉ። አሁን እነሱን ያናገርኩት ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ የፍትሕ ሂደቱን እንደማይጎዳ የሕግ ባለሙያ አማክሬ ነው" ሲል ለችሎቱ አስረድቷል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የተሰጠው መግለጫ ከፍርድ ቤት ውጭ ውሳኔ መስጠት እንደሆነና በሕግ ሂደት ላይ ባለ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት በሕግ ወንጀል መሆኑ መደነገጉን አብራርቷል።

ቀጥሎም "ጋዜጠኛ ተክለሃይማኖት አዳነ የአርቲስቶችን ጠበቃ ስለ መዝገቡ ጠይቆ ጠበቃው 'በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ አልሰጥም' ሲሉ 'ፈሪ ነህ ማለት ነው?' በማለት ተናግሯል፤ ይህም የተሳሳተ አካሄድ ነው።

ማንም ቢሆን መግለጫ መስጠት በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ አያውቅም ተብሎ አይገመትም፤ “የመጣው ይምጣ” በሚል ስሜት የተሰጠ መግለጫ እንደሆነ ስለምናምን፣ ፍርድ ቤቱ በአቤቱታው ላይ የተጠቀሱትን መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥልን" ሲል ጠይቋል።

ዐቃቤ ሕግ ከትላንት በፊቱ ችሎት በጽሑፍ ባቀረበው አቤቱታ፦

• የተከሳሾች የዋስትና መብት ተነስቶ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ፣
• የወንጀል ድርጊቱን ሆን ብለው የፈጸሙት በመሆኑ፣ ጋዜጠኛ ተክለሃይማኖትን ጨምሮ ድርጊቱን ለምን እንደፈጸሙ ተጠይቀው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 457 መሠረት እንዲቀጡ፣
• ፍርድ ቤቱ ቀጥታ የማይቀጣቸው ከሆነ፣ ዐቃቤ ሕግ በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ እንዲመሠረትባቸው እንዲያደርግ፣
• በተላለፈው ቪዲዮ ላይ ይቅርታ ተጠይቆ ከማኅበራዊ ሚዲያ እንዲወርድ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት፣ የሚሉ ነጥቦች ይገኙበታል።

ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ የቀረቡትን አቤቱታዎች መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት 9፡00 ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ገዛ ጌታሁን

11 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.