Logo
EBC
መጥፎውን አዙሪት እንስበር፡ በሌብነት ላይ የሚደረግ የጋራ ትግል
*******************
(የዕለቱ መልዕክት)

ሀገር የምታድገው፣ የምትበለፅገው እና የዜጎቿን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ማረጋገጥ የምትችለው በንፁህ እጆች እና በቅን ልቦች ስትመራ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀመረችው የብልጽግና እና የፈጣን ዕድገት ጉዞ ላይ እንደ ትልቅ ካንሰር እና ማነቆ የተጋረጠው አሳሳቢ ፈተና ሌብነት እና የሙስና ተግባር ነው። ይህ እኩይ ድርጊት በግለሰቦች፣ በንግዱ ማኅበረሰብ፣ በልማት ድርጅቶች እና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ እንደ ምስጥ በመሰግሰግ የሀገርን ሀብት በከፍተኛ ደረጃ በመመዝበር ላይ ይገኛል።

ሙስና እና ሌብነት የሀገርን አጠቃላይ ኢኮኖሚ ከማድማት ባለፈ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲባባስ እና የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋ ያደርጋል። በመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ሰው ሠራሽ እጥረት ፈጥሮ የዋጋ ንረት እንዲባባስ በማድረግ ኅብረተሰቡን ለከፋ ችግር እያጋለጠው ይገኛል። ይህን የጥፋት ተግባር ከሥረ መሠረቱ ነቅሎ ማውጣት አሁን ላይ የሀገር ህልውና፣ ሰላም እና ደህንነት ጉዳይ ሆኗል።

ይህንኑ አሳሳቢ ሀገራዊ ፈተና አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የችግሩን ሥር-ሰደድነት ሲያብራሩ፤ "የተንዛዛ አሰራር ጉቦ ሰጭ ይፈጥራል። ጉቦ ሰጭ ጉቦ ተቀባይ ይፈጥራል። ጉቦ ተቀባይ የተንዛዛ አሰራር ይፈጥራል። ይህ መጥፎ አዙሪት ነው፤ በቀላሉ አንወጣውም። ጉቦኞች እና ሌቦች ባሉበት ሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት ቀርቶ አብሮ መኖርም አስቸጋሪ ይሆናል፤ ካልተረባረብን ያጠፋናል" በማለት አስገንዝበዋል።

ይህን በሽታ ለማከም መንግሥት አሁን ላይ በማያዳግም ሁኔታ ሰፊ የማጽዳት ዘመቻ እና የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ከቁጥጥር ውጭ ለማድረግ በፋይናንስ እና በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ሰርገው በመግባት የኢኮኖሚ አሻጥር ሲፈጽሙ በነበሩ አካላት፣ እንዲሁም በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ እና አስተዳደር መዋቅር ውስጥ በተሰገሰጉ ሌቦች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው።

በተለይም በነዳጅ አቅርቦት እና ሎጂስቲክስ፣ በማዕድን ዘርፍ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ በፋይናንስ ተቋማት እና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዲሁም ከአፈር ማዳበሪያ ግዢ እና ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ላይ ጠንካራ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።

የሕዝብን ሀብት በመመዝበር በተገኙ አመራሮች፣ ነጋዴዎች፣ ደላሎች እና የውጭ ዜጎች ጭምር ላይ የማያዳግም የሕግ ተጠያቂነት እየሰፈነ መሆኑ፤ ሕገ-ወጥ የንግድ ድርጅቶች እና መጋዘኖች እየታሸጉ፣ የተጭበረበሩ የባንክ ሒሳቦች እየታገዱ መሆኑ እንዲሁም አሻጥሩን ከመሰረቱ ለማጋለጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ይበል የሚያሰኝ እና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ተግባር ነው።

ይሁን እንጂ ሌብነትን የማጥፋቱ እና ግልጽነት ያለው ዘመናዊ አሠራርን የመዘርጋቱ ኃላፊነት ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም። መንግሥት የጀመረው ይህ ጠንካራ የሕግ ማስከበር እርምጃ ግቡን እንዲመታ እና ሀገርን ከሕገ-ወጥነት ሙሉ በሙሉ ለመታደግ የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ እና የማይተካ ሚና አለው።

ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ ሕጋዊ መብቱን ለማስከበርም ሆነ አገልግሎት ለማግኘት ጉቦ ከመስጠት መቆጠብ፣ ሌቦችን እና አሻጥር ፈጻሚዎችን ያለ አንዳች ይሉኝታ እና ፍርሃት ማጋለጥ እንዲሁም ከሕገ-ወጦች ጋር ባለመተባበር ከመንግሥት ጎን በጽናት ሊቆም ይገባል።

በተጨማሪም በጅምላ ከመወነጃጀል ወጥተን፣ ሌባውን ለይተን ሌባ በማለት፣ በተቃራኒው በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግለውን ሠራተኛ ደግሞ በማክበርና በማበረታታት ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።

ካልተረባረብን አብሮ መኖርን ጭምር አደጋ ላይ የሚጥለውን ይህን የሙስና እና የሌብነት ደዌ፣ በጋራ ትግላችን፣ በቁርጠኝነታችን እና በማይናወጥ ጽናታችን ማሸነፍ ግድ ይለናል።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

24 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.