Logo
Getu Temesgen
አልማ ለ2019 በጀት ዓመት ከ4.3 ቢሊዮን ብር በላይ የልማት ሀብት ለማሰባሰብ አቀደ
#ethiopia | የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በመገምገም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዱን ያስተዋወቀ ሲሆን፣ የዕቅዱን ስኬት ለማረጋገጥ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍን በሙሉ ማጠናቀቅ እንደሚገባ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መላኩ ፈንታ አሳስበዋል።

በዋና መሥሪያ ቤቱ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ፣ ከ11 ዞኖች የተውጣጡ የማኔጅመንት አባላትና የወረዳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ተሳትፈው በቀጣዩ ዓመት የሚተገበሩ ዋና ዋና የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ተወያይተዋል።

ስትራቴጂክና ኢኖቬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበረ መኩሪያ እንደገለጹት፣ በ2019 በጀት ዓመት ከአባላት 4.3 ቢሊዮን ብር፣ ከዳያስፖራ ከ34 ሚሊዮን ዶላር በላይ እና ከአጋር ተቋማት 55 ሚሊዮን ዶላር የልማት ሀብት ለማሰባሰብ ታቅዷል።

በተያዘው ዕቅድ 2,051 የመማሪያ ክፍሎች፣ 38 የጤና ተቋማት፣ 8 የቴክኒክ ኮሌጅ ወርክሾፖች እና 2 ሸዶች እንዲገነቡ ታቅዷል። ይህን ግዙፍ ዕቅድ ለማሳካት የህዝብ ተሳትፎን ማሳደግ፣ ከአጋር አካላትና ከዳያስፖራው ጋር የተጠናከረ ትብብር መፍጠር ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።

አቶ መላኩ ፈንታ በማጠቃለያ ንግግራቸው፣ በ2019 በጀት ዓመት የዲጂታል ሽግግርን ማፋጠን፣ የአፈጻጸም ጥራትን ማሻሻል፣ የተቋሙን ብራንድ ማጠናከርና ዘላቂ የፋይናንስ አቅም መፍጠር ዋና ትኩረቶች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በመድረኩ መጨረሻ በ2018 በጀት ዓመት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የዞንና የወረዳ አልማ ጽሕፈት ቤቶች፣ እንዲሁም ለተመራጭ ሠራተኞች የማበረታቻ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.