Logo
Getu Temesgen
የCPJ የ2026 ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት አሸናፊዎች ተገለጹ
#ethiopia | የጋዜጠኞችን ጥበቃ ኮሚቴ (CPJ) ለ36ኛ ጊዜ የሚያዘጋጀውን ዓመታዊ International Press Freedom Awards (IPFA) የ2026 ተሸላሚ ጋዜጠኞችን ይፋ አድርጓል።

የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ኅዳር 19 ቀን 2026 በኒውዮርክ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች በድፍረታቸውና በሙያዊ ተግባራቸው ይሸለማሉ።

በዚህ ዓመት ከተሸለሙት መካከል ከሊባኖስ፣ ከኤርትራ፣ ከሀንጋሪ፣ ከኮሎምቢያ እና ከሚያንማር የመጡ ጋዜጠኞች ይገኛሉ።

ክርስቲና አሲ – ሊባኖስ

የAFP ፎቶ ጋዜጠኛ ክርስቲና አሲ በጥቅምት 2023 በእስራኤል–ሊባኖስ ድንበር ዘገባ ስትሰራ በደረሰባት ጥቃት ቀኝ እግሯን አጥታለች፤ የሮይተርስ ጋዜጠኛ ኢሳም አብዳላህም በዚያው ጥቃት ተገድሏል።

CPJ እንደሚለው፣ በዚህ ጉዳይ እስካሁን ተጠያቂ የሆነ አካል የለም። አሲ ከዚያ በኋላ ለጋዜጠኞች ደኅንነትና ለፍትሕ ድምፅ ሆና እየሠራች ነው።

"ኤርትራ 16"

CPJ በዚህ ዓመት ለ25 ዓመታት ያለ ፍርድ ታስረው የቆዩትን "ኤርትራ 16" የተባሉ 16 ጋዜጠኞች በጋራ ሸልሟል።

እነዚህ ጋዜጠኞች በ2001 የግል ሚዲያዎች ከተዘጉ በኋላ ታስረው ሲሆን፣ እስካሁን ክስ አልቀረበባቸውም፣ ፍርድ ቤትም አልቀረቡም። የጤናቸውና የሕይወታቸው ሁኔታ እንኳን በግልፅ አይታወቅም።

ሳቦልች ፓንዪ – ሀንጋሪ

የምርመራ ጋዜጠኛው ሳቦልች ፓንዪ የሩሲያ ተፅዕኖ፣ ሙስናና የፖለቲካ ሥልጣን ላይ በሠራቸው ዘገባዎች የሚታወቅ ሲሆን፣ በ2026 የሀንጋሪ ምርጫ ዋዜማ ከባድ ጫናና የስለላ ክስ ተጋፍጦበታል።

ኤስቴፋኒ ሮድሪጌዝ – ኮሎምቢያ

በአሜሪካ የስፓኒሽ ቋንቋ ሚዲያ Nashville Noticias ዘጋቢ የሆነችው ኤስቴፋኒ ሮድሪጌዝ በ2026 በICE ተይዛ ታስራ ነበር።

CPJ ጉዳዩ በስደተኞች ጉዳይ ላይ በምታደርገው ዘገባ ምክንያት በጋዜጠኞች ላይ የሚደረግ ጫናን የሚያሳይ ነው ብሏል።

ሳይ ዛው ታይክ – ሚያንማር

የMyanmar Now ፎቶ ጋዜጠኛ ሳይ ዛው ታይክ በ2023 የCyclone Mocha ጉዳትን ሲዘግብ ተይዞ 20 ዓመት ከባድ እስራት ተፈርዶበታል።

CPJ እንደሚለው ሚያንማር በዓለም ላይ ጋዜጠኞችን በእስር ከሚያቆዩ አገራት መካከል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የGwen Ifill የፕሬስ ነፃነት ሽልማት

የ2026 Gwen Ifill Press Freedom Award የኤል ሳልቫዶር ጋዜጠኛና El Faro መስራች ካርሎስ ዳዳ ተሸላሚ ሆኗል።

ዳዳ ለዓመታት በሙስና፣ በወንጀለኛ ቡድኖች፣ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና በመንግሥት አሰራር ላይ የምርመራ ዘገባዎችን በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከመንግሥታዊ ጫና የተነሳ በስደት እየኖረ ነው።

CPJ እንደገለጸው፣ የ2026 ተሸላሚዎች የተመረጡት ከፍተኛ አደጋና ጫና ውስጥ ሆነው ለሕዝብ እውነታን ለማድረስ ባሳዩት ድፍረትና ቁርጠኝነት መሠረት ነው።

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.