Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ግብፅ የቀይ ባህር ዘብን ለመቀላቀል ገና እንዳልወሰነች አስታወቀች፡፡ በሳኡዲ አረቢያ አስተባባሪነት ባለፈው ሳምንት በተደረገ አንድ ስብሰባ ቀይ ባህርንና ባብኤል መንደብን ለመጠበቅ በሚል አንድ ጥምር ሀይል መመስረቱ ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚህ ጥምር ሀይል ውስጥ 14 አገራት ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸውን መግለፃቸው የሚጠቅስ መግለጫም ወጥቶ ነበር፡፡ ከእነዚህ አገራት ውስጥ ግብፅ እንዳለችበት በስፋት ተዘግቧል፡፡

ይሁን እንጂ የግብፅ መንግስታዊው አህራም ጋዜጣ በዛሬ ዘገባው አገሪቱ ጥምረቱ ውስጥ ለመግባት ገና ውሳኔ ላይ እንዳልደረሰች ገልጿል፡፡ አንድ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለስልጣንን በምንጭነት የጠቀሰው ዘገባው ‹‹ውሳኔ ላይ ለመድረስ አስፈላጊውን ሂደቶች ለማለፍ የሚያስችሉ ህጋዊና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች እየተመረመሩ ነው›› ብሏል፡፡

ምንጩ እንደገለፁት ማንኛውም የግብፅ ተሳትፎ በተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታን የሚፈልግ ሲሆን ከአገሪቱ ህገ መንግስትና ህጎች ጋር መጣጣም ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም መጠበቅና ተገቢ የሆኑ ተቋማዊ መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚገባውም አስረድተዋል፡፡
በቀይ ባህር ዘብ ጥምር ሀይል ውስጥ የተካተቱ አገራት በጋራ ያወጡት መግለጫ ላይ ግብፅ ስሟ መስፈሩ በጥምር ሀይሉ ውስጥ ለመሳተፍ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ደርሳለች ማለት እንዳልሆነም አብራርተዋል፡፡

5 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.