Logo
FBC
ከመሳሪያ ላንቃ ወደ ሀሳብ ቋንቋ

ለዘመናት የቆየው የመጠላለፍ ፖለቲካና የሴራ ትርክት በኢትዮጵያውያን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ውጥንቅጥና ስብራት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል የተደረጉ የሴራ ፖለቲካ እና የሀሳብ ልዩነት ልፊያዎች ጦሳቸው ዛሬም ድረስ ቅቡልነት ያለው ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ችግር ሆነው ይገኛሉ፡፡

የሴራ እና የመሳሪያ ፖለቲካ ማዕከላዊ ማንጠንጠኛው ሥልጣን ሲሆን፣ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት መሆን የሚገባው ሕዝብ ደግሞ የሴረኞች መቀለጃ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ባለፉት 50 ዓመታት ዴሞከራሲ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ጠፍቶ ስልጣን የህዝብ ማገልገያ ከመሆን ይልቅ መገልገያ እና ህዝብን መጨቆኛ መሳሪያ እንዲሁም በተለያዩ ስርዓቶች የተነሱ የሀሳብ ልዩነቶች ደግሞ እንደ ወንጀል ሲቆጠሩ ቆይተዋል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ እና የቆዩ ቁስሎችን ለማከም እና የሀሳብ ልዩነቶችን በአሰባሳቢ ትርክት ለመቀየር አሁን ላይ ሀገራዊ የምክክር ሂደቶች እና የሐሳብ ልዕልና ሥራዎች ተጀምረው ስራ ላይ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር የጥላቻን፣ የበቀልንና የመከፋፈልን ዑደት በማስቆም ሁሉንም አሸናፊ ለማድረግ የሀሳብ ውይይቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡

ይህ ምክክር በኢትዮጵያን ለዘመናት የተስተዋለውን ፍላጎት በሀይል የማስፈፀም የፖለቲካ ልምምድን በመቀየር ከመሳሪያ ላንቃ ወደ ሀሳብ ቋንቋ የሚያሸጋግር እንደሚሆንም ታምኖበታል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማስጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በሃይለ ቃል ተጀምሮ በሃይል ርምጃ የሚደመደም የፖለቲካ ባሕልን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በመሆኑም የትናንትን ቁስል ከማስታመም አውጥቶ በይቅርታ በማከም፣ ለነገው ትውልድ የአብሮነት መሰረት የሚሆኑ የጋራ ትርክቶችን በመገንባት ከዛሬ አልፎ ለትውልድ የሚቀጥል ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ያስፈልጋል፡፡

ይህም ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት፣ የሐሳብ የበላይነትን በማስፈን እና የጋራ መግባባት በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን ለማረጋገጥ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

በሚኪያስ አየለ

14 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.