Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በሰሜን ቨርጂኒያ በሚገኙ የተለያዩ የስፖርት ማዕከላት (ጂሞች) አካባቢ በተሽከርካሪዎች ላይ ያነጣጠረ ተከታታይ ስርቆት ሲፈጽም ነበር የተባለ የ29 ዓመት ወጣት የአሌክሳንድሪያ ነዋሪ ወደ 200 የሚጠጉ ተደራራቢ የወንጀል ክሶች እንደተመሰረቱበት ተነገረ። ቁምነገር አያልሰው የተሰኘው ይህ ወጣት ለወራት የተደረገን ሰፊ የፖሊስ ክትትልና ምርመራ ተከትሎ ባለፈው ሰኔ 26 ቀን በቁጥጥር ሥር መዋሉን መርማሪዎች አስታውቀዋል።

ፖሊስ እንዳብራራው ተጠርጣሪው ቢያንስ ካለፈው ሚያዝያ 2026 ጀምሮ በፌርፋክስ ካውንቲ፣ በፎልስ ቸርች እና በአካባቢው በሚገኙ መኪና ማቆሚያዎች ላይ ሳይቆለፉ የተቀመጡ ተሽከርካሪዎችን በመለየት የኪስ ቦርሳዎችን፣ ጥሬ ገንዘቦችን፣ የባንክ ክሬዲት ካርዶችን እና ሌሎች የግል ንብረቶችን ሲሰርቅ ቆይቷል። ተጎጂዎች ንብረታቸው መጥፋቱን እንኳ ገና ሳያውቁ፣ ተጠርጣሪው የተሰረቁትን ካርዶች በመያዝ በፍጥነት በአቅራቢያው ከሚገኙ መደብሮች የክፍያ ስጦታ ካርዶችን (gift cards) በመግዛት ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል መፈጸሙ በምርመራው ተረጋግጧል። በፌርፋክስ ካውንቲ ብቻ በሴንትሬቪል፣ በሬስተን እና በማክሊን አካባቢዎች በርካታ ተመሳሳይ የስርቆት ወንጀሎች መፈጸማቸው በፖሊስ መዝገብ ሰፍሯል።

ይህንን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት በፌርፋክስ ካውንቲ ብቻ 32 አዳዲስ ወንጀሎች የተጨመሩበት ሲሆን፣ በአጠቃላይ በተለያዩ አካባቢዎች የፈጸማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ክሳቸውን በአሁኑ ወቅት ወደ 200 አድርሶታል። ተጠርጣሪው ኩምነገር አያልሰው ሐምሌ 14 ቀን በፌርፋክስ ካውንቲ ለቀረቡበት ክሶች በገዛ ዋስትናው ከእስር እንዲለቀቅ የተደረገ ቢሆንም፣ በፎልስ ቸርች ፖሊስ መሥሪያ ቤት በቀረቡበት የተለዩ የወንጀል ክሶች ምክንያት በአሁኑ ወቅት በአርሊንግተን ካውንቲ እስር ቤት በጥበቃ ሥር እንደሚገኝ ታውቋል።

ይህንን መጠነ ሰፊ ስርቆት ተከትሎ የአካባቢው ፖሊስ ነዋሪዎች ንብረቶቻቸውን በጥንቃቄ እንዲጠብቁ አሳስቧል። የኪስ ቦርሳ፣ ስልክ እና የባንክ ካርዶችን መኪና ውስጥ በጭራሽ አለመተው፣ ለአጭር ጊዜ ስፖርት እንኳ ቢሆን መኪናን ሁልጊዜ መቆለፍ እና መስኮቶችን በሚገባ መዝጋት፣ እንዲሁም የግድ መኪና ውስጥ መቀመጥ ያለባቸው ዕቃዎች ካሉ መድረሻው ቦታ ከመደረሱ በፊት በስተጀርባ ዕቃ ማስቀመጫ (ትራንክ) ውስጥ ቀድሞ መደበቅ እንደሚገባ ፖሊስ ምክሩን ለግሷል።

17 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.