Logo
EBC
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ማካሄድ ጀመረ
**********************

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የማጠቃለያ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ ማካሄድ መጀመሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ፣ የዘንድሮው አፈጻጸም የአስተዳደሩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ማጠቃለያ ከመሆኑ አኳያ ካለፉት አምስት ዓመታት አጠቃላይ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ በስፋት እንደሚገመገም ገልጸዋል።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት እንዳስታወቁት፣ ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ያስቀመጣቸውን ስትራቴጂያዊ ግቦች ለማሳካት ታማኝነት እና ቅንነት በተሞላበት መንገድ ያለ ዕረፍት ሲሠራ ቆይቷል።

በዚህም አዲስ አበባን አላስፈላጊ ከሆኑ አጀንዳዎች በማውጣት የሰላም እና የልማት ማዕከል ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በተጨማሪም ከተማዋ ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነባት፣ ጽዱ፣ አረንጓዴ እና ውብ እየሆነች በመምጣቷ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት መሳብ መቻሏን በስኬትነት አንሥተዋል።

ከተመዘገቡት አመርቂ ስኬቶች ባሻገር ዛሬም ያልተፈቱ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በተለይም በአመራሩ ዘንድ የሚታየውን የውጤታማነት ልዩነት፣ እንዲሁም በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት እና የፍልሰት ችግሮች በመድረኩ በጥልቀት እንደሚገመገሙ አስረድተዋል።

ምንም እንኳን በርካታ ስኬቶች ቢመዘገቡም፣ ከሕዝቡ የመልማት ፍላጎት እና ከተያዘው የብልጽግና ግብ አንጻር ገና ብዙ መሥራት እንደሚቀር በመግለጽ፣ የግምገማው ዋና ዓላማ የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስፋት እና ተግዳሮቶችን ለይቶ በመፍታት በቀጣይ በጀት ዓመት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የትኩረት አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ መሆኑን ከንቲባዋ አብራርተዋል።
#ethiopia #ebc #addisababa

22 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.