Logo
Getu Temesgen
“ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሬ እንድመክር ጠርታኛለች”
- የሐመሯ እናት ሙዶ አኮ ያስተጋቡት የሰላም ጥሪ
#ethiopia | በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ከደቡብ ኦሞ ዞን፣ ከሐመር ወረዳ፣ ከካራ ብሔረሰብ የተገኙት ወይዘሮ ሙዶ አኮ ያደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ እናቶችን የሰላም ጥማትና ተስፋ በማንጸባረቅ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።

ለብዙ ዘመናት ሴቶች የታሪክ ተመልካች ብቻ ሆነው መቆየታቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ሙዶ፣ ዛሬ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፃቸውን እንዲያሰሙና ከሀገራቸው ጋር እንዲመክሩ መጋበዛቸው ለርሳቸው ትልቅ ክብርና ደስታ መሆኑን ገልጸዋል።

ወይዘሮ ሙዶ በንግግራቸው፣ ባለመነጋገራችን ምክንያት ያተረፍነው ነገር ቢኖር እንባን፣ መቃብርን፣ ተጨማሪ ጥላቻንና በቀልን ብቻ መሆኑን በቁጭት ተናግረዋል።

ይህ ድምፅ የእሳቸው ብቻ ሳይሆን፣ እስካሁን ማንም ያልሰማቸውና ያልጠየቃቸው የሩቅ እናቶች ሁሉ ድምፅ መሆኑን በማስታወስ፣ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን በኖረችው አለመግባባት የከፈለችውን ዋጋ በግልጽ አስቀምጠዋል።

“እሳት ቤት ቢገነባ ኖሮ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት በገነባች ነበር፤ ነገር ግን ቤት የሚገነባው እጆች ሲተባበሩና ልቦች ሲደማመጡ ብቻ ነው” ሲሉ የአንድነትን አስፈላጊነት ያስገነዘቡት እናት፣ ተመካካሪዎች ይዘውት የመጡትን የቁጣና የጥላቻ ቋጠሮ በመድረኩ ላይ ፈተው እንዲመለሱ አጥብቀው ተማጽነዋል።

በብሔረሰቡ ባህላዊ ልብስ ደምቀው የተገኙት ወይዘሮ ሙዶ፣ “ማን ያሸንፋል?” በሚለው እልህ ውስጥ ከመግባት ይልቅ “ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ” የሚለው የብዙ እናቶች ህልም እውን እንዲሆን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የሰላም እሴትን የሚያጎላው ይህ ንግግር፣ የሀገራዊ ምክክሩን ዋና ግብ በማስታወስ የበርካታ ታዳሚዎችን ልብ የነካና አዎንታዊ ምላሽ ያገኘ ነበር።

24 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.