Logo
EBC
በሕዝባዊ የባለቤትነት መንፈስ የተሰናዳው ታሪካዊ ጉባኤ
********************

ላለፍት አራት ዓመታት ከቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ሰፊና አሳታፊ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ8 የተለዩ አጀንዳዎች ላይ ለመምከር የመጨረሻ የዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ ዋዜማ ላይ ይገኛል።

የምክክር ሂደቱ አካታች፣ አሳታፊ እና ተዓማኒ እንዲሆን በተደረገው ከፍተኛ ጥረት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በሂደቱ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መደረጉ፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሱ ወሳኝ ጥያቄዎችን በተሟላ መንገድ ለመመለስ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡

ነገ በአዲስ አበባ በይፋ ለሚጀመረው ለዚሁ ታላቅ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከመላው ኢትዮጵያ የተወከሉ 4 ሺህ የሕብረተሰብ ክፍሎች (ተመካካሪዎች) በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ በኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ውስጥም ደማቅና ታሪካዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ይህንን ታላቅ ምዕራፍ አስመልክተው የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተመካካሪዎቹ ከማንኛውም ስሜታዊነት በፀዳ መልኩ፣ ኢትዮጵያን ብቻ ማዕከል አድርገው በመወያየት የዘላቂ ሰላምን መንገድ እንደሚያቀኑ ታላቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ልሂቃን በሂደቱ ውስጥ ለሚነሱ ውስብስብ ጉዳዮች ታሪካዊ አመጣጥና የታዩ ክስተቶችን በጥናትና ምርምር አስደግፈው በማቅረብ፣ ተመካካሪዎች ወደ ጋራ መረዳትና ወደ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመሩ የማገዝ ታላቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተመልክቷል።

ነገ በሚከናወነው በዚህ ታላቅ ጉባኤ ላይ የሀገር ውበት የሆነው “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” የመባባል ኩሩ እሴትና የኢትዮጵያውያን ሕብረ-ቀለማት ደምቀው የሚታዩበት ይሆናል። ከሀገሪቱ ልዩ ልዩ ማዕዘናት የተውጣጡ ወገኖች ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው፣ ያለ ምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ለጋራ ዕጣ ፈንታቸው በአንድነት ለመምከር በከፍተኛ ጉጉት ላይ ይገኛሉ።

ለረጅም ዘመናት የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ውጥረቶች መፍትሔ ከውጭ ሲጠበቅ የቆየበት አሮጌ አዝማሚያ ተቀይሮ፣ ዛሬ የችግሮቹ ባለቤቶች የሆኑት ኢትዮጵያውያን ራሳቸው መፍትሔ ፍለጋ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ መሰየማቸው ትልቅ ብሔራዊ ስኬት ነው።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሂደቱ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና ያሳየው የባለቤትነት መንፈስ እጅግ የሚያበረታታ ሲሆን፣ ታሪክ የማይረሳው ሀገራዊ ኃላፊነትም እየተወጣ ይገኛል። ይህ ታሪካዊ ጉባኤ የአንድ ወገን አሸናፊነት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ የጋራ ድል የሚረጋገጥበት፣ ለቀጣዩ ትውልድ ደግሞ የሰላም ውርስ የሚተውበት ደማቅ አሻራ ሆኖ በታሪክ ማህደር ላይ ይመዘገባል።

በብሌን ደምበሎ
#ebc #ethiopia #nationaldialogue #nationalconsensus #inclusiveethiopia

22 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.