Logo
EBC
ምክክር ጥንካሬ የሚሆንባት አዲሷ ኢትዮጵያ
**************

(የዕለቱ መልዕክት)

ኢትዮጵያ ታላቅና ወሳኝ ምዕራፍ ለመክፈት የሚያስችላትን የታሪክ ዋዜማ ላይ ትገኛለች። ዘመናትን የተሻገሩ ውስብስብ ፈተናዎችን፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ስብራቶችን የምንጠግንበት እንዲሁም የታሪክ ጠባሳዎችን ሽረን ወደ ላቀ ከፍታ የምንሸጋገርበት ሀገራዊ ምክክር ለመጀመር እነሆ የቀረን ሁለት ቀናት ብቻ ናቸው።

ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ተራ መድረክ አይደለም ይልቁንም የጋራ እጣ ፈንታችንን በገዛ እጃችን የምንወስንበትና ዛሬ ከተመካከርን ነገን በጋራ እንደምንወርስ የምናረጋግጥበት የህልውናችን ማረጋገጫ ምሰሶ ነው።

«ተመካክረን እንሻገራለን» ስንል የአሁኑን እውነታችንን ፈትሸን ወደ መፍትሔ የምንጓዝበትን ስልታዊ አቅጣጫ ለማመላከት ነዉ። እስካሁን የኖርንበት የቅሬታ፣ የቂም፣ የመገለልና የመጠራጠር ታሪክ ሊያበቃ ይገባል። ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የተኬደባቸው መንገዶች ሁሉ ያተረፉልን ጥፋትንና መከራን ብቻ ስለሆነ ዛሬ ችግሮቻችንን በራሳችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል።

ሀገራዊ ምክክርን እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም በሰለጠነ መንገድ መወያየት መሸነፍ ሳይሆን የጋራ መግባባትን የምንፈጥርበት ብቸኛውና ትክክለኛው የማሸነፊያ መንገዳችን ነው።

እንሻገራለን ስንል አሁን ያሉብን ፈተናዎች ሁሉ ጊዜያዊ መሆናቸውን በጽናትና በተስፋ ማመን፣ ካለንበት አስቸጋሪ ምዕራፍ ወደተሻለ ብሩህ ምዕራፍ ለመድረስ ቃል መግባት ማለት ነው።

የቁርሾ አጥር ፈርሶ የመግባባት ድልድይ የሚሰራበት ጊዜው አሁን ነው። ይህ የሀገራዊ ምክክር መድረክ ትናንት በነበሩ ታሪካዊ ጠባሳዎች ወይም ዛሬ ባሉ ጊዜያዊ ውዝግቦች ላይ ብቻ ተቀርቅረን እንድንቀር አይፈቅድልንም። ይልቁንም ነገን በጋራ እንገነባለን በሚል የረጅም ጊዜ ራዕይ ለቀጣዩ ትውልድ የምናስረክባትን ሀገር እንድንገነባ ያሳስበናል።

ይህ ግንባታ የአንድ ወገን፣ የአንድ ቡድን ወይም የጥቂቶች ብቻ ሊሆን አይችልም። የሁሉንም ዜጎች እውቀት፣ ጉልበት፣ ባህልና አቅም ያካተተ፣ ሁሉም ወገን እኩል ባለቤት የሚሆንበት አካታች ሂደት ነው። ግንባታው ዝም ብሎ ከመመኘት ባለፈ ተግባራዊ ሥራንና የጠንካራ ተቋማትን መመስረት ይጠይቃል። ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ መድረክ ስኬት አንደበታችን ይከፈት፣ ልባችንም ያዳምጥ፤ ምክንያቱም የማዳመጥ ባህል የምክክር መሠረት ነውና።

የኃይል ፖለቲካ አብቅቶ የሃሳብ ገበያ የሚከፈትበት፣ ልዩነት ውበት መሆኑ ታምኖበት ምክክር ጥንካሬ የሚሆንበት ታሪካዊ አጋጣሚ ደርሷል።

በምክክር የምትገነባ ኢትዮጵያ በምንም ዓይነት ማዕበል አትናወጥም። መላው የሀገራችን ሕዝብ፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና የሚመለከታችሁ ተመካካሪዎች ሁሉ ቂምንና መጠራጠርን በማስወገድ፣ ይቅርታን፣ ውይይትንና አብሮነትን በማስቀደም ለዚህ ታሪካዊ ዕድል መሳከት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበርክት፡፡

የጋራ ምክክር፣ የጋራ መፍትሄ፣ የጋራ ሀገር! በምክክር የሚመጣ ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ይሆናል። ይህንን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም፣ ልዩነቶቻችንን ወደ ጥንካሬ፣ ስብራቶቻችንን ወደ ጤና በመቀየር ለሁሉም የምትመችና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ሁላችንም በቁርጠኝነት ልንቆም ይገባል።

ትናንት በታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት፣ ዛሬ ለምናደርገው ጉዞ መሰረት መጣል ይኖርብናል። ሉዓላዊነታችንና አንድነታችን የሚጸናው እርስ በርስ ለመደማመጥ ስንዘጋጅና የጋራ እሴቶቻችንን ስናከብር ብቻ ነው።

ይህ ታላቅ መድረክ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ የዴሞክራሲና የዕድገት ምዕራፍ እንድትሸጋገር የሚያስችላት ቁልፍ ነው። እያንዳንዱ ተመካካሪ የሀገሩንና የወደፊት ትውልድ እጣ ፈንታ በአእምሮው በመቅረጽ፣ አዎንታዊና ፍሬያማ ውይይት ለማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል። ታሪካዊ ግዴታችንን በኃላፊነት ስሜት እንወጣ።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

26 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.