Logo
FBC
ሰላም፤ እንደምን አደራችሁ?

የሀሳብ ልዩነቶቻችን በመነጋገርና በመደማመጥ የምንፈታቸው፣ ማንነቶቻችን ደግሞ ተቻችለን የምንኖርባቸው እንጂ በምንም መልኩ የስጋት ምንጮቻችን ሊሆኑ አይገባም።

ልዩነቶቻችንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ብቸኛውና አስተማማኙ መንገድ ምክክር ነው።

ምክክር የተለያዩ አመለካከቶች በነፃነት ቀርበው የሚስተናገዱበት መድረክ ከመሆኑ ባሻገር፣ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እና በማህበረሰቡ መካከል ጠንካራ የመተማመን ስሜትን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና አለው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ማብራሪያ ላይ እንዳመለከቱት፤ አሁን ላይ “እንመካከር፣ እንወያይ፣ እንፍታ” እየተባለ ያለው ችግር የአሁኑ ትውልድ የፈጠረው አይደለም፤ እኛ ባንፈጥራቸውም እንኳ አሁን ላይ በእኛ ትውልድ ላይ የወደቁትን ታሪካዊና መዋቅራዊ ችግሮች ግን በውይይት የመፍታት የጋራ ኃላፊነት አለብን።

እኛ ያላዋጣንባቸውና ያልመሰረትናቸው ችግሮች ቢሆኑም እንኳ፣ በሕዝቦች መካከል መግባባትን ለመፍጠር፣ መተማመንን ለማስፈንና ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሲባል ተወያይቶ የመፍታት የግድ ይላል።

በጠመንጃ ኃይል እንታገላለን፣ ለሕዝባችን መብት እንቆማለን ብለው የሚያምኑ ኃይሎች በተግባር ግን መልሰው ለማህበረሰቡ ትልቅ የስጋት ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን እያየን ነው።

ይህ ዓይነቱ አካሄድ ወጣቶችን ከትምህርት ገበታቸው ያለያያል፣ ጦርነትና ለጥፋት ያመጣል፣ ሀገርንና ማህበረሰብን ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ይዳርጋል።

በመሆኑም በጦርነትና በኃይል ፍላጎትን ለመጫን መሞከር ትውልድን ከማጥፋት ባለፈ መፍትሄ ሊያመጣ እንደማይችል በተግባር የታየ እውነት ነው።
ማንኛውም ዜጋ በነፃነት የመኖር፣ የመማር እና የመስራት መብቱ እንዲከበር የኢትዮጵያን ሰላም በጋራ ማስጠበቅ ይኖርብናል።

ለልጆቻችን የተሻለች፣ የበለጸገችና የተረጋጋች ሀገር ለማውረስ ስንል የመወያየትና የመደማመጥ ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የሚመክሩላትን፣ የሚወያዩላትንና መፍትሄ የሚያፈልቁላትን ልጆቿን ለመቀበል ተሰናድታለች።

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደዉ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ ከ4 ሺህ ተወካዮች በአዲስ አበባ እየተሰባሰቡ ነው፡፡

ተወካዮቹ በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በዳያስፖራው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ የተመረጡ ወኪሎች ናቸው፡፡

በምክክር ጉባዔው ላይ በሰከነ እና መደማመጥ በተሞላበት ስሜት የልዩነት ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ የሆኑት ተወካዮቹ፤ ለምክክር ጉባዔው ስኬት ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለዋናው ሀገራዊ ጉባዔ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

እነዚህም ፡-

👉 የሀገር ግንባታ

👉 የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣

👉 የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባና ድሬዳዋ ጉዳይ፣

👉 የሃይማኖት ጉዳዮች፣ታሪካዊ ቅሬታዎች እና እርቅ

👉 የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣

👉 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች

👉 ሙስና እና መልካም አስተዳደር እና

👉 የሰላም ግንባታ ናቸው፡፡

30 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.