Logo
EBC
የዘመናት የፖለቲካ ስብራቶችን የመጠገን ሀገራዊ ተስፋ
**********************

ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ታሪካዊ ፈተናዎችን፣ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በጋራ የመመካከር ባህልና "ከዛፍ ሥር" በመቀመጥ የመፍታት የዳበረ የዘመን አይሽሬ እሴት አላቸው። አሁን የተጀመረው አገራዊ ምክክርም ይህንን የትናንት እርሾ መሠረት ያደረገ ትልቅ ሀገራዊ ተስፋ ነው።

ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ የፖለቲካ ስብራቶችን፣ የትርክት መዛነፎችንና የሰላም እጦቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ የታጠቁ ቡድኖችንና ተደማጭነት ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ በማሳተፍ ረገድ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች ሳቢያ የመረጃ አሰባሰብ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም፣ ሂደቱን በቁርጠኝነትና በትዕግሥት በማለፍ አሁን ላይ ለታላቁ ሀገራዊ ጉባኤ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቱን አጠናቋል።

ይህ ታሪካዊ ሁነት የሃሳብና የውክልና አካታችነትን ባረጋገጠ መልኩ ዜጎች አጀንዳዎቻቸውን በነፃነት እንዲያቀርቡና እንዲደማመጡ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ ሂደቱ ፍጹም ግልጽ፣ ገለልተኛና አሳታፊ በሆነ መንገድ መመራቱ ለዘመናት የተንከባለሉ ውስጣዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የሕዝቡን ከፍተኛ ተሳትፎና ትኩረት ሊስብ ችሏል።

ኮሚሽኑ ታሪካዊውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለመጀመር የሚያስችሉትን ዘርፈ-ብዙ የዝግጅት ሥራዎች በስኬት ማጠናቀቁን ተከትሎ፣ ከሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች የተወከሉ የጉባኤው ተሳታፊዎች ወደ አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።

ኮሚሽኑ ወደ መፍትሔ የሚወስድ ድልድይ በመሆን በርካታ ፈተናዎችንና ውጣ ውረዶችን ተቋቁሞ፣ አብረውት ለዘለቁት ኢትዮጵያውያን የልፋቱን ፍሬ ለማስረከብ አሁን በዋዜማ ላይ ይገኛል። መላው የሀገሪቱ ሕዝቦች በከፍተኛ ተስፋ የሚጠባበቁት ይህ ታላቅ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በመጪው ሐምሌ 8 ይጀመራል፡፡

ይህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት በዜጎች መካከል መተማመንን ለመፍጠር፣ የፖለቲካ ሥርዓቱን ለማሻሻል፣ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት እንዲሁም የግጭትና የጦርነት እሳቤዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ፋይዳ አለው። ይሁን እንጂ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ሕዝቡ ራሱ የሂደቱ ባለቤትና ጠባቂ ሲሆን፣ ከመንግሥት ወገን የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የበሰለ ተሳትፎ እንዲሁም ከሌሎች የፖለቲካ ተሳታፊ አካላት የሰላም አማራጭን የመምረጥ ቁርጠኝነት ሲታከልበት ነው።

በብሌን ደምበሎ

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.