Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ‹‹በሞስኮ 1000 ድሮን ስናበር የፑቲን ካልኩሌሽን ይለወጣል›› ሲሉ ዘለንስኪ ገለፁ፡፡ የዩክሬይኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ከፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ከሩሲያ ጋር የሚደረገውን ጦርነት ውጤት የሚለውጠው በአየር የበላይነት መያዝ መሆኑን አስታወቁ፡፡

ፕሬዝደንቱ በጦርነቱ በባህር ሀይልና በምድር ጦር ድል መቀዳጀታቸውን ጠቅሰው ወሳኙና ቀጣዩ በአየር ሀይል የበላይነት መቀዳጀት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሲናገሩም ‹‹በዚህ ጦርነት አሸናፊ የሚሆነው ብልህ እንደሆነ አምናለሁ›› ያሉት ዘለንስኪ ጨምረውም ‹‹በጦር ሜዳ ላይ ጠላት እንዳይንቀሳቀስ ካደረከው በምድር ጦር የበላይነት ይዘህ አቁመኸዋል ማለት ነው፡፡ የሩሲያን መርከቦች በባህር ድሮኖቻችን እንዳይንቀሳቀሱ እንዳደረግነው በባህር ሀይልም የበላይነትን ጨብጠናል፡፡ ስለዚህም አሁን የሚቀረን ሰማዩ ነው›› በማለት አስረድተዋል፡፡

አስከትለውም ‹‹በዚህ በሰማይ ላይ በሚደረግ ውድድር ማን ሰፊ ግዛት አለው የሚለው አይሰራም፡፡ በፊቱንም ተፎካካሪ እንደነበርነው ሁሉ አሁን ወደዚያ ገብተናል›› ካሉ በኋላ ዩክሬይን ረጅም ርቀት ላይ የማጥቃት አቅሟ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልፀው አንድ ድክመት እንዳለባት ግን አልሸሸጉም፡፡ እንዳስረዱትም እሱም ፀረ ሚሳኤል መከላከያ ነው፡፡ ፓትሪዮት ፓክ 3 የተሰኙት እነዚህ መከላከያዎች እያጠሯቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሲናገሩም ‹‹አውሮፓ በዚህ ረገድ የምታሳየውን ቸልተኝነት ማቆም አለባት፡፡ ቴክኖሎጂዎችንና የኢንዱስትሪ አቅሟን ከሌሎች አገራት ጋር መጋራት ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱም ለሁሉም የሚበቃ ፓትሪዮት ሚሳኤል አይኖርም›› ብለዋል፡፡ ዘለንስኪ እንዳብራሩት ፓትሪዮት ሚሳኤሎችን የምታመርተው አሜሪካ ብቻ ስትሆን ይህ ሚሳኤል በአውሮፓ ውስጥ እንዲመረት ፈቃድ ልትሰጥ ይገባታል፡፡ አውሮፓውያንም ከአሜሪካ ይህንን ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረብና መወትወት እንዳለባቸው አሳስበው ዩክሬይን በራሷ መንገድ ለአሜሪካ ጥያቄውን ማቅረቧን አስታውቀዋል፡፡

አገራቸው በክሬሚያ ግዛት ውስጥ የምታደርገውን ረጅም ርቀት ጥቃት እንደምትቀጥል የገለፁት ዘለንስኪ ኢላማቸውም ወታደራዊ ማእከላት፣ የነዳጅ ዴፖዎች፣ የአየር መቃወሚያዎችና የአውሮፕላን መንደርደሪያዎች እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡ ይህንን የሚያደርጉትም ሩሲያ በሀይል ዘርፍና በወደብ መሰረተ ልማቶቿ ላይ ጥቃት ከደረሰባት በኋላ ወታደራዊ ተቋሞቿን በክሬሚያ ስላሰፈረች መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም በዋና ከተማ ሞስኮ ላይ ጥቃት የመቀጠል እቅድ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ እንደፕሬዝደንቱ ገለፃ የክሬሚሊን መሪው ጥቃቱ ሞስኮና ሴንት ፒትስበርግ እስከሚደርስ ድረስ ብዙም አላሳሰባቸውም ነበር፡፡

ጨምረውም ‹‹ፑቲን ክሬሚሊን በጣም ሩቅ ቦታ እንደሆነ አስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሞስኮ ውስጥ ጥቃት መፈፀሙን ሲሰማ ስሜቱ እየገባው መጥቷል›› ካሉ በኋላ በቀጣይነት የሚያደርጉት ጥቃት የበለጠ ፑቲን የጦርነቱን እውነታ እንዲጋፈጡ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አስከትለውም ‹‹በሞስኮ ላይ በመቶዎች አይደለም በሺህ የሚቆጠሩ ድሮኖችን ስናበር የፑቲን ካልኩሌሽን ይለወጣል፡፡ እኛ ወደሞስኮ እጅግ በቀረብን ቁጥር ጦርነቱን ለማቆም አዲስ ምእራፍ ይከፈታል፡፡ ፑቲንም የራሱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ሰላምን ይመርጣል›› በማለት አስረድተዋል፡፡

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.