Logo
EBC
ብዙ እያተረፍንበት ያለው ጊዜያዊ ችግርን ተደጋገፎ የማለፍ ባህላችን
****************

"በብዙ መንገድ ምግብ ተርፎ በሚደፋባት ከተማ ውስጥ በቀን አንድ ጊዜ በተሟላ ሁኔታ ለመመገብ የሚቸገሩ ወገኖቻችንን ማየት የሁላችንም ሕመም እና ሁላችንም ልንወጣው የሚገባ ትልቅ ኃላፊነት ነው።"

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በየረር 30ኛውን የነዋሪዎች የምገባ ማዕከል በመረቁበት ወቅት የተናገሩት ይህ ሀሳብ በከተማዋ ውስጥ ማኅበራዊ ፍትሕን የማንገስን አስፈላጊነት በጉልህ ያሳያል።

ይህ ማዕከል በየረር የተገነባበት ዋናው ምክንያት በሸራተን ሆቴል ማስፋፊያ ልማት ከቂርቆስ አካባቢ ለተነሱ እንዲሁም ከካዛንቺስ ለተዛወሩ ቋሚ ገቢና መጠለያ ያልነበራቸው ዜጎች ድጋፍ ለመስጠት ነው።

"ሕጋዊ ቤት አልነበራችሁም ብለን ነዋሪዎቻችንን መተው ስለማንችል፣ ኃላፊነት ወስደን ያስገባናቸው በርካታ ሰዎች አሉ" በማለት ከንቲባዋ የመንግሥት ልማት ሰው-ተኮር መሆኑን አረጋግጠዋል።

የምገባ ማዕከላት መከፈት በተለይም በልማት ምክንያት ለተነሱና ቋሚ ገቢ ለሌላቸው ዜጎች ንጹሕና ትኩስ ምግብ በነፃ የሚያገኙበት የሕልውና ዋስትና ነው።

እያንዳንዱ ማዕከል አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ የሚመገቡበትና የሚገናኙበት ቋሚ ቤታቸው ከመሆኑም በላይ፣ ወደ ማዕከል መምጣት ለማይችሉ አቅመ ደካሞችም ምግቡ ወደ ቤታቸው የሚላክበት አሠራር የተመቻቸበት ጊዜያዊ ችግርን ተደጋግፎ የማለፊያ ትልቅ ድልድይ ሆኗል።

ይሁን እንጂ የዚህ ስትራቴጂ ዋና ግብ ዜጎችን ሁልጊዜ በማዕከሉ ላይ ጥገኛ ማድረግ ሳይሆን፣ የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ ወደ ቋሚ የሥራ ዕድል ማሸጋገር ነው።

እስካሁን በተከፈቱት 29 የምገባ ማዕከላት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሂደት ወደ ሥራ መግባታቸውና በ30ኛውም የየረር ማዕከልም በርካታ ነዋሪዎች ገና በምረቃው ዕለት በመጋቢነትና በአስተናጋጅነት መቀጠራቸው ለዚህ ማሳያ ነው።

በተጨማሪም በከተማዋ በሴፍቲኔት ተይዘው ከነበሩ መካከል ከ100 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች ራሳቸውን ችለው ዛሬ ላይ ሌሎችን መቅጠር መቻላቸው ከተማዋን ከድህነት ለማውጣት የተያዘው ሰው-ተኮር ልማት በተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ያረጋግጣል።

ይህ በከተማዋ የተጀመረው ጊዜያዊ ችግርን ተደጋገፎ የማለፍ ባህል የመንግሥት ሸክም ብቻ ሳይሆን ባለሀብቶችና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ከገቢያቸው ላይ ቀንሰው የሚሳተፉበት የማኅበራዊ ኃላፊነት ውጤት ነው።

ማዕከላቱ በዘላቂነት ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማስቻል የምገባ ኤጀንሲው የቁሳቁስና የደረጃ ክትትል የሚያደርግ ሲሆን፣ ጉድለት በተገኘ ጊዜም ከመንግሥት በጀት እንደሚሟላ ታውቋል።

ከተማን በዘላቂነት ማበልጸግ የሚቻለው ሕንጻዎችን በመገንባት ብቻ ሳይሆን ሌት ተቀን ጠንክሮ በመሥራት፣ እርስ በርስ በመደጋገፍና ለአቅመ ደካማ ወገኖች በመትረፍ ጭምር መሆኑን የ30ኛው የምገባ ማዕከል መከፈት ትልቅ ማሳያ ነው።

በሔዋን ጌታቸው
#ethiopia #addisababa #communitysupport #socialjustice #ebc

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.