Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘውን ኩምሩክ ከተማ ‹‹በጥቂት ሰአታት ውስጥ›› እንደሚቆጣጠር አስታወቀ፡፡ አልሻረቅ አልአውሳት የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው በሌተና ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልብሩሀን የሚመራው የሱዳን ጦር ሀይል በብሉ ናይል ግዛት ውስጥ በሚገኘው ኩምሩክ ከተማ አካባቢ ከፍተኛ ሀይል እያስገባ ይገኛል፡፡ ወታደራዊ ምንጮቹን ዋቢ ያደረገው ዘገባው እንዳለው ሀይል ማጠናከር ያስፈለገው በተፋላሚው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ታጣቂዎች ምሽግ ላይ እያደረሰ ያለውን የመድፍ ድብደባ ተከትሎ ነው፡፡ በተጨማሪም ድሮኖችን በመጠቀም በተፋላሚው ታጣቂዎች ላይ ጥቃቱን መቀጠሉን ያስታወቀው ዘገባው ይህም የጦር ሀይሉ ወደፊት እንዲገፋ እንዳስቻለው አስታውቋል፡፡

ይህንን ተከትሎም አሁን በከተማው ዙሪያ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ የምድር ጦር ፍልሚያ መጀመሩን ጠቅሷል፡፡ ለዚህ ፍልሚያ እንዲረዳው ሀይሉን በማጠናከር ላይ የሚገኘው የሱዳን ጦር ወታደራዊ ምንጮች ጨምረው እንደገለፁት ጦርነቱ በሚቀጥሉት ሰአታት ውስጥ ኩምሩክ ከተማ ውስጥ ዘልቆ እንደሚገባ እምነት አሳድረዋል፡፡ ስለጉዳዩ ከዜና አውታሩ የተጠየቁት የኩምሩክ ከተማ ገዥው አብዱል አቲ አል ፋቂ ሲናገሩ ‹‹ወታደራዊ ድሉ እየተቃረበ ነው›› ካሉ በኋላ ይህ ፍልሚያ በብሉ ናይል ግዛት ውስጥ ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉን ጠራርጎ ለማስወጣት ‹‹የመጨረሻው አውደ ግንባር ነው›› ብለዋል፡፡ ጨምረውም የሱዳን ጦርና አጋሮቹ የመንግስትን ክብር ለመመለስና የተነጠቁ አካባቢዎችን ለማስመለስ ቁርጠኛ ሆነው እየተፋለሙ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ እንደዘገባው ካለፈው መጋቢት ወር አንስቶ በብሉ ናይል ግዛት ውስጥ የሱዳን ጦር በአንድ በኩል እንዲሁም ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉና አጋሮቹ በሌላ በኩል ሆነው ከባድ ጦርነት እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

ይህንን ተከትሎም ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ከኢትዮጵያና ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰነውን ኩምሩክ ከተማ ለመቆጣጠር ችሎ ነበር፡፡ የከተማው ገዢ የሆኑት አል ፋቂ ለአልሻረቅ አልአውሳት በሰጡት መግለጫ በአካባቢው ያለው የሰብአዊነት ሁኔታ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ነው፡፡ በአካባቢው ለወራት በዘለቀው በዚህ ጦርነት ወደ100 ሺህ ያህል ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የመብራትና የውሀ መሰረተ ልማቶችንና የጤና አገልግሎት መስጫዎችን በማውደሙ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡ እንደዘገባው ኩምሩክ ከተማ በደቡብ ምስራቃዊ ሱዳን በብሉናይል ግዛት ውስጥ የሚገኝና ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር የሚዋሰን ነው፡፡

ይህ ከተማ የግዛቱ ዋና ከተማ ከሆነው ዳዝሚን በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ይገኛል፡፡ ከተማው በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የአቅርቦት ሰንሰለት ያለበት በመሆኑ ትልቅ ወታደራዊ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ እንዳለውም አስረድቷል፡፡
1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.