Logo
EBC
የኢትዮጵያ የማዕድን አብዮት - ከ0.2 በመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ ወደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ሞተርነት
*************************

የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ለበርካታ አሥርት ዓመታት በፖሊሲ ክፍተት፣ በሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ እና በተደራጀ ብክነት ምክንያት እምቅ አቅሙ ሙሉ በሙሉ ተዘንግቶ ቆይቷል።

ዛሬ ላይ ግን በአዲሱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከሀገራችን 5 ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ በመሆን ታሪካዊ ትንሣኤውን አብስሯል።

ሀገራችን ስትገነባው የቆየችው በመንግሥት ከፍተኛ ወጪ ላይ የተመሠረተ እና ለዕዳ ተጋላጭ ያደረጋት የኢኮኖሚ ሞዴል ፈታኝ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።

ይህን በማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ በዋጋ ግሽበት እና በውጭ ምንዛሬ እጥረት የተተበተበ ማነቆ በዘላቂነት ለመቅረፍ የተተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ማዕድንን ከመረሳት ወደ ብሔራዊ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽነት በውጤታማነት አሸጋግሮታል።

ይህ መዋቅራዊ ለውጥ በመረጃ እና በቁጥር ሲመዘን እጅግ አስደናቂ ሆኖ እናገኘዋለን። በ2010 ዓ.ም የማዕድን ዘርፍ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) የነበረው ድርሻ 0.2 በመቶ ብቻ ነበረ። በ2017 ዓ.ም ይህ ቁጥር የ7 እጥፍ ብልጫ በማሳየት ወደ 1.4 በመቶ ማደግ ችሏል።

በተለይም በወርቅ ምርት እና ኤክስፖርት ላይ የታየው ለውጥ በታሪካችን ወደር የማይገኝለት እመርታ ነው።

ባህላዊ የማዕድን ቁፋሮን ወደ መደበኛ የንግድ ሥርዓት በማስገባት በተደረገው ስኬታማ የፖሊሲ ማሻሻያ፣ የሀገራችን የወርቅ ኤክስፖርት ገቢ ከ100 ሚሊዮን ዶላር ወደ 3.48 ቢሊዮን ዶላር በማደግ የ35 እጥፍ ጭማሪ አስመዝግቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ የተገበረው በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት ደግሞ አምራቾች ምርታቸውን በመደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት እንዲያቀርቡ በማድረግ ለዚህ ስኬት ትልቅ ሞተር ሆኗል።

በሌላ በኩል "ኢትዮጵያ ታምርት" በተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ የማዕድን ዘርፉ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ጋር በጥብቅ በመተሳሰሩ፣ ገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት ከፍተኛ ድል ተመዝግቧል።

ለአብነት ያህል የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካን መመልከት በቂ ነው። ይህ ዘመናዊ ፋብሪካ በየዓመቱ የከሰል ድንጋይ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት እንዲተካ አስችሏል።

በተመሳሳይ የኖራ ድንጋይ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ ከ17 በመቶ ወደ 75 በመቶ ከፍ ማለቱ፣ እንደ ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ እና ሙገር የመሳሰሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች የማምረቻ ወጪያቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ አድርጓል።

ይህ በማዕድን ዘርፉ የታየው ዕድገት በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ሰፊ ማኅበራዊ ፋይዳንም አምጥቷል።

በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪው ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎቻችን ቀጥተኛ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ከ4 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ኑሯቸውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዚህ ዘርፍ ላይ መስርተዋል።

በአጠቃላይ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የማዕድን ዘርፉን ከድቅድቅ ጨለማ አውጥቶ የሀገራችንን የኢንዱስትሪ ሽግግር የሚያፋጥን ሞተር አድርጎታል።

ይህ የማዕድን ዘርፍ ስኬት ዘርፉ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ዕውን የሚያደርግ አስተማማኝ ምሰሶ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

በለሚ ታደሰ
#ethiopia #mining #madeinethiopia #economicreform #goldexport #ebc

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.