Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ መምህራን የመኖሪያ ቤት ችግር መፍትሄ ይሆናል ተብሎ የተቋቋመው የመምህራን ማህበር የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክት፣ ተስፋ ከማድረግ ይልቅ ለመምህራኑ የብስጭት እና የእዳ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ዘ-ሐበሻ ሰምቷል።

በፕሮጀክቱ መሰረት መምህራን እንደየቤቱ ስፋት (ባለ አንድ፣ ባለ ሁለት፣ እና ባለ ሶስት መኝታ ክፍል እንዲሁም ስቱዲዮ) ቅድመ ክፍያ እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል። ለምሳሌ፣ ባለ ሶስት መኝታ ክፍል ቤት ለማግኘት የተመዘገቡ መምህራን 680,000 (ስድስት መቶ ሰማንያ ሺህ) ብር የቅድመ ክፍያ ፈጽመዋል። ይህንን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለመክፈል፣ በርካታ መምህራን ባላቸው አነስተኛ አቅም ንብረታቸውን መሸጥ እና መበደርን ጨምሮ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸው ተገልጿል።

መምህራኑ ቅድመ ክፍያውን ከፈጸሙ በኋላ፣ የቤቶቹ ግንባታ በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አማካኝነት እንደሚከናወን ቢገለጽም፣ እስካሁን ግንባታው ሊጀመር አልቻለም። ለዚህ መዘግየት በምክንያትነት የተጠቀሰው የቤቶች ልማት እና ግንባታውን የሚያካሂዱት ኮንትራክተሮች የውል ስምምነት አለመፈጸማቸው ነው። ኮንትራክተሮቹ ወደ ስራ ለመግባት ውሃ እና መብራት ወደ ግንባታ ስፍራው እንዲገባ የሚጠይቁ ሲሆን፣ የቤቶች ልማት በበኩሉ ይህንን ማሟላት ባለመቻሉ እና ውል ለመፈረም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ፕሮጀክቱ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ሆኗል። መምህራኑ ክረምቱ ሰበብ ሊሆን እንደሚችል ቢገምቱም፣ ውሃ እና መብራት ለማስገባት እንዲሁም የውል ስምምነት ለመፈጸም ክረምት እንቅፋት ሊሆን እንደማይችል ለዘ-ሐበሻ ጠቁመዋል።

መምህራኑ ላነሱት ቅሬታ ምላሽ ለማግኘት እና የፕሮጀክቱን እጣ ፈንታ ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና አመራሮች ብንደውልም፣ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም። ይህ የመንግስት ዝምታ ጉዳዩን ይበልጥ አጠራጣሪ ያደረገው ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መምህራን የከፈሉት ገንዘብ እና የመኖሪያ ቤት ተስፋቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም። ይህ ሁኔታ መንግስት ለዜጎቹ፣ በተለይም ለመምህራን የሰጠውን ቃል አለማክበሩን እና በፕሮጀክቶች ላይ ያለውን የተጠያቂነት ክፍተት በግልጽ የሚያሳይ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.