Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) በኒውጀርሲ በተካሄደው እጅግ አጓጊ እና ትንፋሽ አስቋራጭ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ፣ የዘመናችን አደገኛው ግብ አዳኝ ኤርሊንግ ሀላንድ ለኖርዌይ ብሔራዊ ቡድን በድጋሚ ደምቆ አምሽቷል። ኖርዌይ ሴኔጋልን 3 ለ 2 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ከምድቧ ወደ 32ቱ ጥሎ ማለፍ መቀላቀሏን በይፋ አረጋግጣለች።

ጨዋታው ሲጀመር በተወሰነ መልኩ የተቀዘቀዘ ቢመስልም፣ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል ግን የሴኔጋሉ አምበል ካሊዱ ኩሊባሊ የሰራውን አስደንጋጭ ስህተት ተጠቅሞ ተቀይሮ የገባው ማርከስ ፔደርሰን ኖርዌይን ቀዳሚ አደረገ። በዚሁ አጋማሽ የ25 ዓመቱ ሀላንድ በተወሰነ መልኩ ተዳፍኖ የነበረ ሲሆን፣ እንዲያውም የሴኔጋሉን ግብ ጠባቂ ኤዶዋርድ ሜንዲን አታሎ ካለፈ በኋላ ያገኘውን ክፍት ጎል ቋሚ ገጭቶበት በማባከን ተመልካቹን አሳዝኖ ነበር።

ነገር ግን የሀላንድ ዝምታ ከእረፍት መልስ ብዙም አልዘለቀም! 48ኛው ደቂቃ ላይ አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ ሰንጥቆ ያቀበለውን ወርቃማ ኳስ በፍጥነት ተረክቦ መረብ ላይ በማሳረፍ መሪነቱን ወደ ሁለት አሳደገ። ይህች ጎል ሀላንድን የኖርዌይ የምንግዜም የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ አድርጋዋለች። ሴኔጋሎች በበኩላቸው በቀላሉ እጅ አልሰጡም፤ በእስማኢላ ሳር አማካኝነት አንድ ጎል ቢመልሱም፣ ሀላንድ አላስቻላቸውም። ከአምስት ደቂቃ በኋላ፣ ብዙም በማይጠቀመው ቀኝ እግሩ አየር ላይ እንዳለ በበረራ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ታኮ ሲገባ ስታዲየሙ በጩኸት ተናጋ! ሀላንድ ማቆሚያ እንደሌለው በድጋሚ አረጋገጠ።

የጨዋታው ማብቂያ ላይ የክሪስታል ፓላሱ የክንፍ ተጫዋች እስማኢላ ሳር በጭማሪ ሰዓት ሁለተኛ ጎሉን አስቆጥሮ ጨዋታውን እጅግ አጓጊ አደረገው። እንዲያውም በመጨረሻዎቹ ሴኮንዶች ሳር በግንባር ገጭቶ የሞከራት ኳስ በትንሹ ወደ ውጪ ባትወጣ ኖሮ ሴኔጋል አቻ የምትሆንበት እድል ነበራት። በመጨረሻም የስታሌ ሶልባከን ስብስብ የሆነችው ኖርዌይ ውጤቱን አስጠብቃ ወጥታለች።

ይህ አጥቂ በእውነትም ጫና የሚባል ነገር አይፈጠርበትም! በሁለት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ብቻ አራት ጎሎችን አስቆጥሯል—ይህ ማለት በታሪክ ማንኛውም የኖርዌይ ተጫዋች ካስቆጠረው ጎል እጥፍ ማለት ነው! ከዚህም ባሻገር ለብሔራዊ ቡድኑ በተሰለፈባቸው ተከታታይ 12 የውድድር ጨዋታዎች ላይ ጎል ያስቆጠረ ሲሆን፣ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ ቢያንስ ሁለት ሁለት ጎሎችን ማግባት ችሏል። የትናንቱ ብቸኛ አስገራሚ ነገር ቢኖር ሀላንድ ሀት-ትሪክ ሰርቶ አለመውጣቱ ብቻ ነው!

በዚህ ውጤት መሰረት ኖርዌይ ከኃያሏ ፈረንሳይ ጋር ከምድብ 9 ማለፏን አረጋግጣለች፤ አርብ ዕለትም የምድቡን አንደኛ ለመለየት ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ ይፋለማሉ። በሌላ በኩል ሴኔጋል ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ቀጭን ተስፋዋን ለማለምለም፣ በመጨረሻው የምድብ ጨዋታዋ ኢራቅን የግድ ማሸነፍ ይጠበቅባታል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.