Logo
FastMereja
በሣውላ ከተማ የ8ኛ ክፍል ፈተና ለተማሪ ሊፈተን የገባ መምህርና ተማሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ ።

በሣውላ ከተማ ኩስቲ ቁጥር አንድ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ፈተና ለተማሪ ሊፈተን ከተማሪ ጋር ተመሳስሎ የገባ መምህርና ተማሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ገለፀ

ተማሪን ወክሎ ከመምህር ስነ ምግባር ባፈነገጠ ተግባር ተሳተፈ የተባለው ከቡልቂ ከተማ ሙሉ ፩ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣው መምህር እስራኤል አሰፋ የማንዴላ ርቀት ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው አብነት እንዳለን ክልላዊ ፈተና ሊፈትን ሲል በተደረገ የኮማንድ ፖስት ክትትል በቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን የገለጹት የከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያዕቆብ በተላ ናቸው።

ፈተናውን ከኩረጃና ስርቆት የፀዳ ለማድረግ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የኮማንድ ፖስት አባላቱ ድርጊቱን በማጋለጥ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠታቸው ሊፈተን የገባው መምህርና ፈተናውን አሳልፎ ከሰጠው ተማሪ ጋር በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል።

የሣውላ ከተማ ፓሊስ አዛዥ ተወካይ ምክትል ኢንስፔክተር ሞገስ ሞኔ በበኩላቸው ተማሪውንና መምህሩን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመው በማዕከሉ እየተሰጠ ያለው ፈተና ፍጹም ሠላማዊ እና በተረጋጋ መንገድ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ምርመራ በአስቸኳይ አጣርቶ በአቃቤ በኩል ለፍርድ ቤት አቅርቦ ለማስወሰን እየሠራ መሆኑንም ምክትል ኢንስፔክተር ሞገስ ሞኔ ገልጸዋል።

ምንጭ ሣውላ ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽን

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.