Logo
YenetaTube
በአማራ ክልል የየአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(አዴን ) ታጣቂዎች ሁለት ወረዳዎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸው ተነገረ

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሚንቀሳቀሱት 'የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ' (አዴን) ታጣቂዎች፤ አበርገሌ እና ፃግብጂ የተባሉ ሁለት ወረዳዎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን የአካባቢው አስተዳደርና ነዋሪዎች ገለጹ።

ከሁለት ዓመት በፊት ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት ፈርሞ የነበረው አዴን ካለፈው ሚያዝያ ወር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ወረዳዎቹን መቆጣጠሩን የዞኑ ፀጥታ መምሪያና ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።

የቡድኑ ኃላፊዎች በበኩላቸው ወረዳዎቹን መቆጣጠራቸውን ቢያምኑም፣ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል የሚለውን መረጃ ግን አስተባብለዋል።

እንደ ነዋሪዎችና የዞኑ አስተዳደር ገለጻ፣ በአበርገሌ ወረዳ ሚያዚያ 12 ቀን የተቀሰቀሰውና በከባድ መሣሪያ የታገዘው ውጊያ ቀኑን ሙሉ የፈጀ ሲሆን፤ የአዴን ኃይሎች ከ"ህወሓት ታጣቂዎች" ጋር በመቀናጀት ጥቃት ሰንዝረዋል። ይሁን እንጂ የአዴን የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ካሴ ከህወሓት ጋር መጣመራቸውን ያስተባበሉ ሲሆን፣ ግጭቱ የተቀሰቀሰው የመንግሥት ኃይሎች "አመራሮቻችንን አፍነው ለመውሰድ በመሞከራቸው ነው" ብለዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ከሁለት ሳምንት በፊት ግንቦት 18 ቀን አዴንና የትግራይ ኃይሎች በቅንጅት የፃግብጂ ወረዳን መቆጣጠራቸውን ነዋሪዎች ቢናገሩም፤ የአዴን ኃላፊዎች ግን መንግሥት "የሀራ መሬት" (የትግራይ ሰላም ኃይል) ታጣቂዎችን አምጥቶ ውጊያ በመክፈት ስምምነቱን አፍርሷል ሲሉ ይከሳሉ። የዞኑ ፀጥታ መምሪያ ግን ስለ እነዚህ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ተጨባጭ መረጃ እንደሌለው አስታውቋል።

ግጭቱን ተከትሎ ስጋት ያደራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለው ወደ ዞኑ ዋና ከተማ ሰቆጣ ተፈናቅለዋል። በአበርገሌ ወረዳ ከሚገኙ ቀበሌዎች የአንዱ ሊቀመንበር እንደገለጹት፣ ከቀበሌው ነዋሪ ግማሽ የሚጠጋው (ከ3 ሺህ በላይ ሕዝብ) የተፈናቀለ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከወረዳው ወደ 10 ሺህ የሚጠጋ ሕዝብ ሳይፈናቀል እንዳልቀረ ጠቁመዋል።

ተፈናቃዮቹ በሰቆጣ ከተማ ጎዳናዎችና በተጀመሩ ሕንፃዎች በረንዳ ላይ ተጠልለው እንደሚገኙና የምግብ ድጋፍ ባለማግኘታቸው በልመና እየኖሩ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ታጣቂዎቹ የግዴታ ምለመላ፣ የገንዘብና የቀለብ መዋጮ እየጠየቁ አስገድደዋቸዋል ብለዋል።

ከተወሰኑ የረድኤት ድርጅቶች (እንደ ወርልድ ቪዥን) ከተደረገ አነስተኛ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ውጪ፣ እስካሁን ከተደረገላቸው ምዝገባ ባለፈ ተጨባጭ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳልቀረበላቸው ተፈናቃዮቹ ተናግረዋል።

ይህ አዲስ ግጭት በ2016 ዓ.ም. የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በአካባቢው ሰፍኖ የነበረውን መረጋጋት ያደፈረሰ ሲሆን ለስምምነቱ መፍረስ ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ እየተካሰሱ ይገኛሉ።

BBC

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.