Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ታዋቂው የእስልምና ሃይማኖት መምህር ኡስታዝ ያሲን ኑሩ በምስራቅ አርሲ ዞን በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት አጥብቀው በማውገዝ የተሰማቸውን ጥልቅ እና መሪር ሐዘን ገልጸዋል። ኡስታዙ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት "ምነው የተከበረው የሰው ልጅ ህይወት እንዲህ ረከሰ?" በማለት በመገረም፣ ድርጊቱን የዜጎችን ነፍስ ለርካሽ ዓለማዊ ግብ ማሳኪያነት ለመጠቀም የሚደረግ "ሀገር አጥፊ" ተግባር ሲሉ በጽኑ ኮንነውታል።

የብዝሃ ሃይማኖት እና ብሔር ብሔረሰቦች እናት የሆነችውን ሀገራችንን ሰላም ለማናጋት፣ እንዲሁም ለዘመናት የተገነባውን የሕዝቦች የጠበቀ ትስስር ለመበጠስ ያሰፈሰፉ ኃይሎች የሚያደርጉትን ጥፋት ያወገዙት ኡስታዝ ያሲን፤ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል። የሚመለከታቸው አካላት ይህንን የሀገር ዕድገት የሚገታ እኩይ ተግባር በማስቆም፣ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ሰብዓዊ መብት ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ዜጎች በሰላም ወጥተው ስለመግባታቸው መተማመኛ የሌላቸውን ሀገር ወደፊት የመራመድ እና የማደግ ዕድሏ የመነመነ መሆኑን ያስገነዘቡት ኡስታዙ፣ "ስለ ሀገሬ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል የሚል ሁሉ 'ሀይ' ሊል ይገባል" ሲሉ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

"እንዲህ ዓይነቱን አስነዋሪ ድርጊት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሕዝቦች መካከል አለመተማመንን የሚዘሩ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች የጉዳዩን አደገኛነት ተገንዝበው ቆም ብለው እንዲያስቡ እና ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ " ኡዝታዙ አበክረው መክረዋል።
ፈጣሪ የተበዳዮችን እምባ እንዲያብስ፣ ለበዳዮችም የእጃቸውን እንዲሰጣቸው እና በሀገሪቱ ፍትሕን እንዲያሰፍን ጸሎት በማድረግ መልእክታቸውን አጠቃልለዋል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.