Logo
EBC
ሀገርነት የሚገነባው ከመውሰድ ይልቅ በመስጠት ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
********************

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1447ኛው የዒድ አል አድሐ (ዐረፋ) በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ ዜጎች ከግል ጥቅማቸው ይልቅ ለሀገርና ለሉዓላዊነት ቅድሚያ በመስጠት መስዋዕትነት ሊከፍሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የዐረፋን በዓል ታሪካዊ ዳራ በማስታወስ፣ ወስነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እስማኤልን ለመስዋዕትነት ለማቅረብ ያሳዩትን ቆራጥነት እንደ ትልቅ ማሳያ ጠቅሰዋል።

"ሀገር የምትገነባው ከራስ ጥቅም በላይ በሚያስቡ እና ከግላዊ ፍላጎታቸው በላይ ለመፈጸም በቆረጡ ዜጎች ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያም ጠንካራና ጽኑ ሀገር መሆን የምትችለው የሚወዱትን ነገር ሳይቀር ለሀገራቸው ለመሠዋት ዝግጁ የሆኑ ዜጎች ሲበዙላት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም "የለመድናቸው፣ የምንወዳቸው፣ የራሳችን ገንዘብ ያደረግናቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ከእነዚህ የሚበልጥ ዓላማ ግን አለ፤ እሱም 'ሀገርነት እና ሉዓላዊነት' ይሰኛል" በማለት፣ ሉዓላዊነት የሚጸናው በፈተና ሳይወድቁ በመቆምና በወጀብ ሳይናወጡ መጓዝ በመቻል እንደሆነ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የበለጸገች ሀገር ሆና እንድትወጣ የሚመኙ ሁሉ ምኞታቸውን በተግባር እንዲገልጹ፣ ድህነትን ለማሸነፍና የሀገርን ክብር ለመመለስ ሌት ተቀን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

"ሀገር መውደዳችን ከልብ ከሆነ መስዋዕት ለመሆን አናመንታ" ሲሉም ጠንካራ ሀገራዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
#eidaladha #pmabiyahmed #ethiopia #patriotism #nationalunity #ethiopianbroadcastingcorporation

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.