Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) እግር ኳስ የድሃ እና የሀብታም ልዩነትን የሚያጠፋ ልዩ ስፖርት ነው። ከሪዮ ዴጄኔሮ እና ናይሮቢ መንደሮች እስከ ሞናኮ እና ቤቨርሊ ሂልስ የቅንጦት መንደሮች ድረስ ልጆች እግር ኳስን ሲጫወቱ ማየት የተለመደ ነው። ይህ ስፖርት ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የተነሱ በርካታ ተጫዋቾችን የሀገር ጀግና እና የዓለም ምልክት ለማድረግ ችሏል።
የምንጊዜም ምርጥ 10 የዓለም ዋንጫ ጀግኖችን በተመለከተ ለበርካታ አስርት ዓመታት አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል። ውይይቱ እግር ኳስ እስካለ ድረስ የሚቀጥል ቢሆንም፣ ከ2026ቱ የዓለም ዋንጫ በፊት የተመረጡትን የምንጊዜም ምርጥ 10 የዓለም ዋንጫ ጀግኖች ዝርዝር እንደሚከተለው አቅርበነዋል፦

10. ዚነዲን ዚዳን (ፈረንሳይ)

ከምንጊዜም ምርጥ እና አነጋጋሪ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዚዳን፣ በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ሀገሩ ፈረንሳይ ዋንጫውን ስታነሳ በፍጻሜው ጨዋታ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። በ2006ቱ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ላይ በጣሊያኑ ተጫዋች ማትራዚ ላይ በፈጸመው ታሪካዊ የጭንቅላት ምት (Headbutt) በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢወጣም፣ የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። ለፈረንሳይ በ108 ጨዋታዎች 31 ግቦችን ሲያስቆጥር፣ በአሰልጣኝነትም ከሪያል ማድሪድ ጋር ሦስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አግኝቷል።

9. ጂሚ ግሪቭስ (እንግሊዝ)

እንደ ቦቢ ሙር ያሉ ታላላቅ ተጫዋቾች ቢኖሩም፣ በእንግሊዝ ደጋፊዎች ዘንድ እንደ ጂሚ ግሪቭስ የተወደደ አልነበረም። በ1962ቱ የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ላይ ወደ ሜዳ የገባን ውሻ በመያዝ ታዋቂነትን ያተረፈ ሲሆን፣ በ1966ቱ የእንግሊዝ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ስብስብ ውስጥም ቁልፍ ተጫዋች ነበር። በእንግሊዝ ብሔራዊ ማሊያ 6 ጊዜ ሃት-ትሪክ የሰራ ሲሆን፣ ክብረወሰኑም እስካሁን አልተሰበረም።

8. ፌረንች ፑሽካሽ (ሀንጋሪ)

የሀንጋሪ ወርቃማ ትውልድ ቡድን አምበል የነበረው ፑሽካሽ፣ ለሀንጋሪ ባደረጋቸው 85 ጨዋታዎች 84 ግቦችን አስቆጥሯል። ሀንጋሪ በእሱ መሪነት በ1950ዎቹ እጅግ አስፈሪ ቡድን የነበረች ሲሆን፣ በ10 ዓመት ውስጥ የተሸነፈችው የ1954ቱን የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ብቻ ነበር። በአጠቃላይ በሙያው ባደረጋቸው 705 ጨዋታዎች 702 ግቦችን አስቆጥሯል።

7. ሎታር ማቲዎስ (ጀርመን)

ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን 150 ጨዋታዎችን በማድረግ ክብረወሰን የያዘው ማቲዎስ፣ በአምስት የዓለም ዋንጫዎች ላይ የተሳተፈ ሲሆን፣ በ1990 ምዕራብ ጀርመን ዋንጫውን እንድታነሳ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በዓለም ዋንጫ ታሪክ ብዙ ጨዋታዎችን (25) በማድረግም ክብረወሰን ይዟል። ታላቁ ማራዶና "በህይወቴ ከገጠሙኝ ተጫዋቾች ሁሉ እጅግ ከባዱ እሱ ነበር" ሲል መስክሮለታል።

6. ሚሮስላቭ ክሎዘ (ጀርመን)
በስፖርታዊ ጨዋነቱ (Fair play) ወደር የማይገኝለት ክሎዘ፣ በዓለም ዋንጫ ታሪክ 16 ግቦችን በማስቆጠር የምንጊዜም ከፍተኛው የግብ አስቆጣሪነት ክብረወሰን ባለቤት ነው። በአራት የዓለም ዋንጫዎች ላይ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን፣ በ2014 የዓለም ዋንጫን ከጀርመን ጋር አንስቷል። ለሀገሩ በ137 ጨዋታዎች 71 ግቦችን መረብ ላይ አሳርፏል።

5. ሮናልዶ ናዛሪዮ (ብራዚል)

"ዘ ፌኖሜኖን" በመባል የሚታወቀው ሮናልዶ፣ ገና በ17 ዓመቱ በ1994 የዓለም ዋንጫን አሸንፏል። በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች ሲባል፣ በ2002ቱ ፍጻሜ ደግሞ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ብራዚልን ለድል አብቅቷል። በዓለም ዋንጫ ታሪክ 15 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፤ ፍጥነቱ፣ ኳስ የመቆጣጠር ችሎታው እና አጨራረሱ ወደር አይገኝለትም።

4. ፍራንዝ ቤከንባወር (ጀርመን)

በእግር ኳስ ታሪክ እንደ ተጫዋችም ሆነ እንደ አሰልጣኝ የዓለም ዋንጫን ካነሱ ሦስት ሰዎች አንዱ ነው። በ1974 የዓለም ዋንጫውን የጀርመን አምበል ሆኖ ሲያነሳ፣ በ1990 ደግሞ በዋና አሰልጣኝነት አሸንፏል። ተከላካይ ቢሆንም ለሀገሩ 14 ግቦችን በ103 ጨዋታዎች አስቆጥሯል።

3. ዮሃን ክራይፍ (ኔዘርላንድስ)

ባሎን ዶርን ሦስት ጊዜ ያሸነፈው ክራይፍ፣ የ"ቶታል ፉትቦል" ፍልስፍና አባት ነው። እግር ኳስን ከጉልበት ስፖርትነት ወደ ጥበብ እና ውበት የቀየረ ታላቅ ፈጣሪ ነበር። በ1974 ኔዘርላንድስን እስከ ፍጻሜ ያደረሰ ሲሆን፣ እርሱ ግብ ባስቆጠረባቸው ጨዋታዎች ሀገሩ ተሸንፋ አታውቅም (በ48 ጨዋታዎች 33 ግቦች)።

2. ዲዬጎ ማራዶና (አርጀንቲና)

በእግር ኳስ ታሪክ አቻ ከሌላቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው። በ1986 የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ በእንግሊዝ ላይ ያስቆጠራት "የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ጎል" እና በውዝግብ የምትታወቀው "የፈጣሪ እጅ" ግቡ አይረሱም። በዛው ዓመት አርጀንቲናን ለዓለም ዋንጫ ድል አብቅቷል።

1. ፔሌ (ብራዚል)

ከብራዚሉ ፔሌ የበለጠ የተሳካ የእግር ኳስ አዶ የለም። የዓለም ዋንጫን ሦስት ጊዜ (1958፣ 1962 እና 1970) ያነሳ ብቸኛው ተጫዋች ነው። ለብራዚል በ92 ጨዋታዎች 77 ግቦችን አስቆጥሯል። ታዋቂነቱ ከማየሉ የተነሳ በ1969 በናይጄሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት እርሱ የሚጫወትበትን ጨዋታ ለማየት ሲባል ጦርነቱ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጎ ነበር። ፔሌ እግር ኳስን ወደ ላቀ የጥበብ ደረጃ ያደረሰ የምንጊዜም ምርጥ ተጫዋች ነው።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.