Logo
FBC
የዋንጫው ባለቤት ዛሬ ይታወቃል ወይስ…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ባለቤት የሚሆነውን ክለብ ሊወስን የሚችለው የቦርንማውዝ እና ማንቼስተር ሲቲ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይደረጋል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ የምሽቱን ጨዋታ አቻ ካጠናቀቀ ወይም ሽንፈት ካስተናገደ አርሰናል አንድ ጨዋታ እየቀረው የ2025/26 ሻምፒዮን መሆኑን ዛሬ ምሽት ያረጋግጣል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ የዋንጫ ተስፋውን እስከ መጨረሻው ሳምንት ለማስቀጠል የምሽቱን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብቷል፡፡

በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከሲቲ ጋር እንደሚለያዩ የሚጠበቁት ፔፕ ጋርዲዮላ በምሽቱ ጨዋታ የሚጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ይፋ ሆኗል፡፡

ጂያንሉጂ ዶናሩማ፣ ማቲያስ ኑኔዝ፣ ኩሳኖቭ፣ ማርክ ጉሂ፣ ኒኮ ኦ'ሬሊ፣ ሮድሪ፣ ኮቫቺች፣ በርናርዶ ሲልቫ፣ ሴሜንዮ፣ ዶኩ እና ሀላንድ በቋሚነት ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡

ባለሜዳው ክለብ በርንማውዝ ፔትሮቪች፣ ትሩፌርት፣ ሴኔሲ፣ ስኮት፣ ኢቫኒልሰን፣ አዳምስ፣ ስሚዝ፣ ታቨርኔር፣ ክሩፒ ጁኒየር፣ ሂል እና ራያንን በቋሚ አሰላለፍ ይጠቀማል፡፡

ጨዋታው ምሽት 3 ሰዓት ከ30 የሚጀመር ሲሆን፥ የ47 ዓመቱ አንቶኒ ቴይለር በመሃል ዳኝነት ይመሩታል፡፡

በሌላ ጨዋታ በለንደን ደርቢ ቼልሲ በሊጉ ለመቆየት 1 ነጥብ የሚፈልገውን ቶተንሃም ሆትስፐር ምሽት 4 ሰዓት ከ15 በስታምፎርድ ብሪጅ ያስተናግዳል፡፡

26 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.