Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደ እሳት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት መንሸራተት፣ ጎርፍ፣ የኬሚካል መፍሰስ እና የአውሮፕላን አደጋዎች ላሉ ድንገተኛ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የመጀመሪያ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ "የኢትዮጵያ እሳት እና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት"ን የሚያቋቁም ደንብ አጸደቀ። የዚህ አዲስ ተቋም ተጠሪነት ለብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ይሆናል።

አዲሱ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ሀገራዊ የአደጋ ምላሽ መስፈርቶችን እና አሰራሮችን ከማዘጋጀት ባለፈ፣ በድንገተኛ አደጋ ምላሽ ዘርፍ ለተሰማሩ ግለሰቦች እና ተቋማት የሙያ ፈቃድ ይሰጣል። የሰው ሀይሉም ከመደበኛ ሰራተኞች በተጨማሪ ከፊል-ወታደራዊ እና የቅድመ-ሆስፒታል ህክምና ባለሙያዎችን ያካተተ ይሆናል።

ተቋሙ ሀገራዊ የአደጋ መረጃ ቋት የማደራጀት እና የልምምድ ስራዎችን የማከናወን ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፤ ስራውን በብቃት ለመወጣት እንዲችልም አነስተኛ አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮች፣ ጀልባዎች እና የሳተላይት መገናኛ ሬዲዮዎችን ጨምሮ ዘመናዊ ቁሳቁሶች ይሟሉለታል። የተቋሙ በጀት ከመንግስት እና በቅርቡ ከተቋቋመው የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ የሚሸፈን ይሆናል። ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንም የደንቡን መጽደቅ የሀገሪቱን የአደጋ መከላከል አቅም የሚያሳድግ ትልቅ እርምጃ ነው ሲል አድንቆታል።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.