Logo
EBC
ከስኬት ማማው በስተጀርባ ያሉት ብርቱ እናቶች
************************

እናትነት በቃላት የማይገለጽ ጥልቅ ፍቅር ብቻ ሳይሆን፣ የሕይወት መጀመሪያ ትምህርት ቤት እና የማያልቅ የጥንካሬ ምንጭ ነው።

ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ በታላቅ የክብር ስፍራ ላይ የምናያቸው ስመ-ጥር ግለሰቦች፣ ለደረሱበት የስኬት ማማ ትልቁን መንገድ የጠረጉላቸው በጸሎትና በጽናት ከጎናቸው የቆሙት እናቶቻቸው መሆናቸውን ታሪካቸው ምስክር ነው።

ለአብነት ያህል "የአፍሪካዋ ቴሬዛ" በመባል የሚታወቁት አበበች ጎበና፣ በረሃብ ለተጎዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት እናት ለመሆን የገዛ ትዳራቸውንና ምቾታቸውን መስዋዕት በማድረግ ለሀገር የሚጠቅሙ በርካታ ዜጎችን አፍርተዋል።

በዓለም መድረክ ስማቸው በጉልህ የሚጠቀሱ ታላላቅ አትሌቶች እና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ታዋቂ ሰዎች ለዛሬው ዝናቸውና ክብራቸው መሠረቱ በገጠር ሕይወት ውስጥ በታታሪነትና በሥነ-ምግባር ያሳደጓቸው እናቶቻቸው መሆናቸውን በኩራት ይናገራሉ።

በጥበቡ ዓለምም ብንመለከት፣ ድምፃዊ ሮፍናን በ"ነፀብራቅ" አልበሙ ላይ የእናቱን ምክር አካቶ ያቀረበበት መንገድ፣ የእናቶች ቃል ለስኬት ያለውን ጉልህ ሚና ያሳየበት አጋጣሚ ነው።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶም ቢሆን፣ ለዛሬው ዝናው እናቱ በልጅነቱ የከፈለችው መስዋዕትነት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ደጋግሞ ይገልጻል።

ታላቁ የፈጠራ ሰው ቶማስ ኤዲሰን ዓለምን በብርሃን የሞላ ግኝት እንዲያበረክት፣ እናቱ ናንሲ ኤዲሰን በልጃቸው ላይ የነበራቸው ጽኑ እምነት እና በቤት ውስጥ ያስተማሩት ትምህርት መሠረት ሆኖታል።

እነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች እንጂ፣ ስማቸው በታሪክ መዝገብ ላይ ባይሰፍርም ለልጆቻቸው ሕልም ሲሉ የራሳቸውን ፍላጎት መስዋዕት ያደረጉ እልፍ እናቶች አሉ።

ከአንድ ስኬታማ የጥበብ ሰው፣ ሳይንቲስት ወይም ባለሙያ በስተጀርባ፤ ዓለም ሁሉ ፊቱን ሲያዞር "ትችላለህ" ብላ ተስፋ የሰጠችና የደከመች ብርቱ እናት ሁሌም ትገኛለች። እናትነት የዓለም ሁሉ ስኬት መነሻ ነችና ሁሌም ልትከበር ይገባታል።

በልዩ እሸቱ
#mothersday #successstories #ethiopia #inspiration

25 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.