Logo
EBC
ኢትዮጵያ ታምርት ፡ በራስ ላብ፣ የራስ ምርት
********************

(የዕለቱ መልዕክት)

ለዘመናት በገቢ ምርቶች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የኖረ ኢኮኖሚ የራስን ሉዓላዊነት ሙሉ አያደርገውም። የሀገር ብልጽግና መሠረቱ ደግሞ በባዕድ እጅ የሚሰፈር ሳይሆን በራስ ላብና ጥረት የሚመረት መሆኑ አያጠያይቅም።

ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የተጋረጡብንን የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፈተናዎችን በመሻገር የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ከአንቀላፋበት ቀስቅሶ ሕይወት ዘርቶበታል። ይህ ንቅናቄ ዝም ብሎ የቃላት ጋጋታ ሳይሆን “ላብ ካልፈሰሰ፣ አዝመራ የለም” የሚለውን እውነታ በተግባር ያሳየ፣ የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነታችንን ያበሰረ ብርቱ የለውጥ ማዕበል ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የለውጡ ጉዞ ውጤታማነት በቁጥር ብቻ ሳይሆን በገበያ ድርሻም ተረጋግጧል። ከሦስት ዓመት በፊት 30 በመቶ ብቻ የነበረው የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ድርሻ ዛሬ 41 በመቶ ደርሷል። ይህ መሻሻል ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን፣ ሥራ አቁመው የነበሩ 830 ኢንዱስትሪዎችን ዳግም ወደ ማምረት በመመለስና 325 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን በአዲስ መንፈስ ወደ ሥራ በማስገባት የተገኘ ድል ነው።

በተለይም ከለውጡ በፊት 8 ሺህ ገደማ የነበሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ዛሬ 26 ሺህ መድረሳቸው፣ ኢኮኖሚው ከመንግሥት መርነት ወደ ግሉ ዘርፍ መዘዋወሩንና የዜጎች የሥራ ፈጠራ ተነሳሽነት መጎልበቱን ያሳያል። “ታጥቦ ጭቃ” መሆንን አቁመን፣ በገዛ ደጃችን ተኪ ምርቶችን እያመረትን መገኘታችን የኢኮኖሚ ነፃነታችን ማሳያ ነው።

የግብርናና የኢንዱስትሪ ትስስርም ሌላኛው የንቅናቄው ስኬት ነው። ቡና፣ ሻይና ሩዝ በገበሬው እጅ ብቻ ተመርተው ሳይሆን በፋብሪካዎች እሴት ተጨምሮባቸው ለዓለም ገበያ መቅረባቸው የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍ አድርጎታል።

“ሳይቀደሙ መቅደም” እንዲሉ መከላከያና ፖሊስ ከውጭ በውድ ምንዛሬ የሚገዛ የደንብ ልብስን ትተው ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካታቸው፣ እንዲሁም የብቅል ገብስ ዘርን እዚሁ ማምረት መቻላችን 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬን ለማዳን አስችሏል። በተጨማሪም የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳና የምግብ ኢንዱስትሪዎች እምቅ አቅማቸውን እያወጡ ይገኛሉ።

የጥራት መንደር አበርክቶ ደግሞ ለዚህ ሁሉ ስኬት ሞተር ነው። በዓመት 5.2 ሚሊዮን ቶን ምርትን የመመርመር አቅም ያለው ይህ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የጥራት ደረጃቸው እንዲጠበቅ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት ይህ ተቋም በዓለም የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያለንን ተሳትፎ የሚያጎለብት የብልጽግናችን መተማመኛ ነው።

በአጠቃላይ "ኢትዮጵያ ታምርት" ከሸቀጥ ግብይት ባለፈ "የኢትዮጵያ ይሸጥ" የሚል ኩሩ እሳቤን ይዟል። 235 ሺህ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የወጣቶችን ሕይወት የቀየረው ይህ ንቅናቄ፣ ቁልፍ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የኢኮኖሚ ነፃነታችንን የሚያጸና ነው። በጋራ ካመረትንና የራሳችንን ምርት ከተጠቀምን፣ የብልጽግና ጉዟችን የማይቀለበስ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ታምርት፣ ኢትዮጵያ ትበልጽግ!

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል
#ethiopia #industry #manufacturing #importsubstitution #madeinethiopia #ethiopiadelivers #ebc #ebcdotstream

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.