Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ፣ በ1990ዎቹ ክለቡን በማሰልጠን ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፉትን ትውልደ ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ስሎቦዳን ሚቾን ዳግም ወደ ኢትዮጵያ አስመጥቷል።

ፈረሰኞቹ በፕሪሚየር ሊጉ ከውጤት ርቀው መቆየታቸው፣ በተለይም ባለፈው ሳምንት በነበረው ተጠባቂው የሸገር ደርቢ በባላንጣቸው ኢትዮጵያ ቡና የ3 ለ 1 ያልተጠበቀ ሽንፈት ማስተናገዳቸው የክለቡን አመራሮች አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ አስገድዷቸዋል። ይህንን የደርቢ ሽንፈት ተከትሎም፣ የቀድሞ አሰልጣኙን በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ የማምጣቱ ሂደት እንደተፈጸመ ታውቋል።

አሰልጣኝ ሚቾ ዛሬ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ከክለቡ ተጫዋቾች እና አሁን ካለው የአሰልጣኝ ስታፍ ጋር ትውውቅ አድርገዋል። ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርገውን ጨዋታም በመከታተል የቡድኑን ወቅታዊ አቋም በቅርበት ይገመግማሉ ተብሎ ይጠበቃል። አሰልጣኙ ዛሬ በነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአርባምንጭ ከተማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ላይ፣ በስታዲየም ተገኝተው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ እና ምክትል አሰልጣኝ መሀል ተቀምጠው ጨዋታውን ሲከታተሉ ታይተዋል።

በቀጣይ ቀሪ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ልምምድ፣ የአጨዋወት ፍልስፍና እና የተጫዋቾች አሰላለፍ ምርጫ ሙሉ በሙሉ በአሰልጣኝ ሚቾ የሚመራ ይሆናል። ይሁን እንጂ አሰልጣኙ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እስካሁን ህጋዊ ምዝገባ ያላደረጉ በመሆናቸው፣ በጨዋታ ቀናት ከፊት ለፊት (በሜዳው ዳር) ወጥተው መመሪያ ከመስጠት ይልቅ፣ ከጀርባ ሆነው የክለቡን ስራዎች በበላይነት እንደሚመሩ ከወጣው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ይህ የፈረሰኞቹ ያልተጠበቀ እርምጃ ክለቡን ወደ ቀድሞ የድል መንገዱ ይመልሰው ይሆን? የፕሪሚየር ሊጉ ቀሪ ጨዋታዎች የሚመልሱት ይሆናል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.