Logo
FastMereja
"የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊባኖስን አይጨምርም" ኔታንያሁ

​#fastmereja I የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አሜሪካ ከኢራን ጋር ያደረገችውን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደግፉም፣ ስምምነቱ እስራኤል በሊባኖስ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ እንደማያካትት በይፋ አስታወቁ። ይህ መግለጫ የወጣው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ "ተኩስ አቁሙ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ስፍራ ተግባራዊ ይሆናል" ካሉ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

​ኔታንያሁ በኤክስ (X) ገጻቸው ባሰፈሩት መግለጫ፣ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ለአሜሪካና ለእስራኤል የኒውክሌርና የሚሳይል ስጋት እንዳትሆን የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል። ሆኖም ግን "የሁለት ሳምንቱ የተኩስ አቁም ሊባኖስን አይጨምርም" በማለት እስራኤል በሰሜን በኩል ከሂዝቦላ ጋር የምታደርገውን ውጊያ እንደማታቆም ግልጽ አድርገዋል።

​ሊባኖስ ወደዚህ ጦርነት የገባችው እ.ኤ.አ መጋቢት 2 ቀን የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ መገደላቸውን ተከትሎ ሂዝቦላ ጥቃት በመሰንዘሩ ነበር። በእስራኤል ጥቃት እስካሁን ከ1,500 በላይ ሊባኖሳውያን መገደላቸውና 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ መፈናቀላቸው ይነገራል።

​ኔታንያሁ ይህን ይበሉ እንጂ፣ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሰላም የሂዝቦላ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኢራን የሚመራ በመሆኑ፣ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በኢራንና በአሜሪካ መካከል የሚደረገው ድርድር ለሊባኖስ እጣ ፈንታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ዛሬ ረቡዕ ጠዋት በደቡብ ሊባኖስ ስሪፋ እና ሳዲቂን በተባሉ አካባቢዎች የአየር ጥቃት መፈጸሙን የሀገሪቱ ብሔራዊ የዜና ወኪል ዘግቧል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.